የስክሪን ሱሰኛ ነዎት? እንግዲያውስ እነዚህን ይሞክሩ

ስልክ፣ ታብሌትና ኮምፒውተር ከፍቶ የሚመለከት ሰው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ድንገት ሳያስቡት ስልክዎን ከኪስዎ መዘው ያወጣሉ? ከኢንተርኔት መላቀቅ አይችሉም? ማኅበራዊ ድረ ገጹ ሱስ ሆኖቦታል? በቲቪ መስኮት ላይ እንዳፈጠጡ መሽቶ ይነጋል? ነግቶስ ይመሻል?

ይህ የእርስዎ ብቻ ችግር አድርገው አይውሰዱት። በዓለም ላይ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከተንቀሳቃሽ ስልኮቻቸው ጋር ተጣብቀው አሉ። ይሰቃያሉ፣ እንቅልፍ ያጣሉ፣ ስልኮቻቸውን አለመነካካት አይችሉም።

ባል ከሚስት፣ እናት ከልጅ፣ አባት ከቤተሰቡ ጋር አፍ ለአፍ ገጥሞ ማውራት ተስኖታል። በሽታ ነው። ክፉ በሽታ። የስክሪን በሽታ።

በዚህ በኮሮናቫይረስ ዘመን ደግሞ ብሶበታል። አይፎን ከያዙ በቀን ስንት ሰዓት በስክሪንዎ ላይ እንዳፈጠጡ ይነግርዎታል። በእውነቱ ይደነግጣሉ። በኮሮናቫይረስ ምክንያት የሰዎች የስክሪን ላይ የመደቀን አባዜ በ30 ከመቶ መጨመሩን አንድ ጥናት አሳይቷል።

እውነት ለመናገር ስልክዎ ላይ የሚያጠፉት አብዛኛው ሰዓት የሚያስቆጭ ነው። መጻሕፍት ቢያነቡ የተሻለ እንደሚጠቀሙ እሙን ነው።

ከልጆችዎ ጋር ቢጫወቱ የተሻለ እንደሚደሰቱ አሌ አይባልም። ወጣ ብለው ዱብ ዱብ ቢሉ የተሻለ ጤና እንደሚያገኙ አያጠራጥርም። ታዲያ ከስልክዎ ጋር ለምን አይፋቱም?

የስክሪን ሱስ በጊዜ ሃይ ካልተባለ እያሳሳቀ የሚወስድ ደዌ ነው። ኾኖም ከሱሱ መፈወስ እንዲህ የዋዛ አይደለም። የስክሪን ሱስን መስበር ቁርጠኝነት ይጠይቃል።

አሁን የጤና ባለሞያዎችን እያሳሰበ ያለው ሰዎች ከስልኮቻቸው ጋር መለያየት ባለመቻላቸው ለአእምሮ ጤና ችግር የመጋለጥ ዕድላቸው እየመጨመረ መምጣቱ ነው።

ይሄ ነገር ይመለከተኛል ካሉ ዘላቂ መፍትሄ እስኪያገኙለት ድረስ እነዚህን አምስት መንገዶች ይከተሉ።

1. እረፍት ይውሰዱ

ዶ/ር ቼትና ካንግ በናይንቲንጌል የአእምሮ ሆስፒታል የቴክኖሎጂ ውጤቶች ሱስ ማገገሚያ ክፍል ሐኪም ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት ምን ያህል ሰዓት በስክሪን ላይ አፍጥቶ መዋል ነው ጤናማ ለሚለው ቁርጥ ያለ መልስ የለም። ሆኖም ለሰዓታት ከቆዩ በሽታ ነው። እስኪ በትንሽ በትንሹ እነዚህን ለማድረግ ይሞክሩት።

ለምሳሌ አንድ ሰዓት ስልክዎ ላይ የሚያፈጡ ከሆነ ቢያንስ 15 ደቂቃ እረፍት ይውሰዱ። 30 ደቂቃ ከሆነ ቢያንስ 7 ደቂቃ ፋታ ያድርጉ።

ይህ የሚመከረው እንዲሁ አይደለም። ለተከታታይ ሰዓት ስክሪን ማየት መጀመሪያ ዓይንን ስለሚጎዳ፣ ቀጥሎ ራስ ምታትንን ስለሚያስከትል፤ ቀጥሎ ደግሞ ድብርትን ስለሚቀሰቅስ ነው።

ዶ/ር ቼትና ካንግ እንደሚሉት ዘለግ ላለ ሰዓት ያለ እረፍት ስክሪን ማየት ቀስ በቀስ ራስን ወደ መጥላት፣ በራስ ላይ ቁጥጥርን ወደ ማጣትና በመጨረሻም የአእምሮ መላላትን ያመጣል። ስለዚህ እባክዎ ቢያንስ የ15 ደቂቃ እረፍት መውሰድን ይለማመዱ።

2. ሱስዎን ምን እንደሚቀሰቅሰው ይለዩ

አንዳንድ ጊዜ እንዴት እጅዎ ተንደርድሮ ኪስዎ ውስጥ እንደገባ ለራስዎ እንኳን ሳይገርምዎ ይቀራል? ሴቶች ሳያስቡት ቦርሳቸው ውስጥ ሰተት ብለው ይገባሉ። ስልካቸውን ለምን እንደፈለጉት እንኳ አያውቁም። ወንዶችም እንዲሁ።

ለምን ይመስልዎታል? ነገሩ ሱስ ነው!

አንዳንዴ ከሱሱ ይልቅ ወደ ሱሱ የሚመሩንን ነገሮች መፈተሸም ተገቢ ነው።

ለምሳሌ ድብርት፣ ሥራ መፍታት፣ የስሜት መታወክ ሊሆን ይችላል። በተለይ ደግሞ ብቸኝነት ከተሰማን አጫዋች እንፈልጋለን። በዚህ ጊዜ እጃችን ተንደርድሮ ስልክ መዞ ያመጣል።

ስለዚህ ሱሱን ከማከምዎ በፊት ስሜትዎ ላይ ይስሩ። ለምሳሌ የሚሰማዎትን ስሜት ለጓደኛዎ ያጋሩት። ስክሪን ላይ ከሚያፈጡ በድምጽ ያውሩት። ወይም ወረቀት ላይ ይጻፉት፣ ወይም መጻሕፍት ገልጠው ያንብቡ። ያ መጥፎ ስሜት ሲጠፋ የስልክ ሱስዎ ረገብ ማለት ይጀምራል።

በጨለማ ውስጥ ስልኳን የምትመለከት ሴት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

3. የስልክ መመልከቻ ሰዓት ይወስኑ

ሁላችንም ጠዋት ተነስተን የመጀመሪያ ተግባራችን ስልክ ላይ ማፍጠጥ ከሆነ አደጋ አለው። መጀመርያ እጅዎን ወደ ስልክዎ እንዲዘረጉ የሚያደርጉ ምክንያቶችን ይለዩ፤ ከዚያ እነርሱ ላይ ቁጥጥር ያድርጉ።

ለምሳሌ ከእንቅልፍ የሚቀሰቅስዎትን ደወል ስልክዎ ላይ ከመጫን በሌላ ደውል ይተኩት፤ ስልክዎ ከቀሰቀሰዎ ስልክ ላይ የማፍጠጥዎ ዕድል ከፍተኛ ስለሚሆን።

ወደ መኝታ ሲገቡ ስልክዎን ይዘው ባይገቡ ይመረጣል። ለምን መሰልዎ? አንደኛ ከስክሪን የሚወጣው ጨረር ለዓይን ጤና ጸር ነው። ለእንቅልፍ እጦትም ይዳርግዎታል። የእንቅልፍዎን ጥራትም ይቀንሰዋል።

4. ከስልክዎ ይልቅ ሰው ይምረጡ

ከሰዎች ጋር ለመገናኘት ስልካችን ሁነኛው መንገድ ነው። ዙም፣ ፌስታይም፣ ስካይፕ፣ ሃውስፓርቲ የተሰኙት የማኅበራዊ መገናኛ የስክሪን ቡና ቤቶች አሁን የሰው ለሰው ግንኙነትን እየተኩ ነው።

ዶ/ር ቼትና ካንግ እንደሚሉት በዚህ መንገድ ሰዎችን ማግኘት ብቸኛው ወይም ዋንኛው ዘዴ መሆን አይኖርበትም። ሰዎችን በአካል ማግኘት እጅግ የማይተካ ስሜትን ይሰጣል። ያን ይሞክሩ። ይሄ ታዲያ በኮሮናቫይረስ ጊዜ ማለት እንዳልሆነ መቼስ ለእርስዎ አይነገርም።

5. እስኪ ስልክዎን እርግፍ አድርገው ወደ ደጅ ይውጡ

አንዳንድ ጊዜ ከስልክ በፊት ሕይወት እንዴት ነበር የተኖረው ብለው አልጠየቁም? እርግጥ ነው ከተንቀሳቃሽ ስልክ መፈጠር በፊት የሰው ልጅ ምድር ላይ ኖሯል።

ያን ለማወቅ ለምን ስልክዎን ቤት አስቀምጠው ትንሽ ንፋስ ተቀብለው፣ በሰፈር ወዲያ ወዲህ ብለው፣ ጓደኛዎን አግኝተው፣ ሻይ ቡና ብለው፤ ጋዜጣ አንብበው አይመጡም? ሁሌም ባይሆን አንዳንዴ።

አሁን እኮ ነገሩ እየከበደ ነው። ከስልካችን ቴሌቪዥን ይቀበለናል፤ ቴሌቪዥን እያየንም እጃችን ስልካችንን መነካካቱን አይተውም፤ ከዚያ ደግሞ ላፕቶፕ አለ፤ ከዚያ ኔትፍሊክስ ወደ አልጋችን አንከብክቦ ይወስደናል። ከስክሪን ወደ ስክሪን ሆነ ነገሩ ሁሉ።

ዶ/ር ቼትና ካንግ እንደሚሉት ይሄ ነገር ለጤና ጥሩ አይደለም። መጀመርያ አይናችንን ቀስ በቀስ ደግሞ አእምሯችንን ይነካል።

በሳምንት አንድ ቀን ጨርሶዉኑ ስክሪን ላይ የማያፈጡበት ቀን ለምን አይመድቡም? ያን ማድረግ ከቻሉ ጥሩ ጅማሮ ነው።

ከመጻሕፍት ጋር አንድ ጊዜ በፍቅር ከወደቁ ደግሞ ስክሪን ትዝም ላይልዎ ይችላል።