ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በቪዲዮ ምክንያት ሁለት ታዳጊ ፓኪስታናውያን በቤተሰብ አባል ተገደሉ
በሰሜናዊ ፓኪስታን የሚኖሩ ሁለት ታዳጊዎች ኢንተርኔት ላይ በተሰራጨ አንድ ቪዲዮ ምክንያት "የክብር ግድያ" በሚባለው ሁኔታ ተገድለዋል።
በፓኪስታን ውስጥ በማህበረሰቡ ዘንድ "አስነዋሪና ክብርን የሚያዋርድ" ስራ ሰርተዋል የሚባሉ ሴቶች "የክብር ግድያ" በሚባለው መንገድ ይሞታሉ።
በአብዛኛው በቤተሰብ አባላት የሚገደሉ ሲሆን እነዚህም ታዳጊዎች በአንድ ቤተሰብ አባል በጥይት ተገድለዋል ተብሏል።
ግድያው የተፈፀመው የተፈፀመው ሁለቱ ሴቶች ከአንድ ወንድ ጋር የሚያሳይ ቪዲዮ በማህበራዊ ሚዲያዎች መውጣታቸውን ተከትሎ እንደሆነ ፖሊስ አስታውቋል።
ፖሊስ ሁኔታውን ለመርመር ራቅ ብላ ወደምትገኘው ቦታ በርካታ የፖሊስ ኃይልን አሰማርቷል።
ግድያው የተፈፀመው በዚህ ሳምንት ሐሙስ ሲሆን የድንበር ከተማ በምትባለው ሻም ፕሌይን ጋርዮም መሆኑንንም የፓኪስታን ሚዲያ የፖሊስን ሪፖርት ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።
በሚዲያው ዘገባ መሰረት ለግድያው ተብሎ የተሰጠው ምክንያት የ16ና የ18 አመት ታዳጊዎቹ እንዲሁም አንዲት እድሜዋ ያልተጠቀሰና ከግድያው የተረፈች ታዳጊ ጋር ሰው በሌለበት ቦታ አንድ ወንድ አብሯቸው ሆኖ ቪዲዮ ሲቀርፅ የሚያሳይ ነው።
ቪዲዮው ወሲባዊ ይዘት አለው የተባለ ሲሆን 52 ሶኮንዶችን ብቻ ነው የሚያሳየው።
ቪዲዮው የተቀረፀው ባለፈው አመት ሲሆን በቅርብ ሳምንታትም ነው ማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ወጥቶ ብዙዎች እንደተጋሩት ከፍተኛ የፖሊስ ኃላፊ ለጋዜጣው ተናግረዋል።
"በአሁኑ ሰአት ዋነኛ ስራችን ሶስተኛዋን ታዳጊ እንዲሁም ግለሰቡ ላይ ወንጀል ከመፈፀሙ በፊት በህይወት ማቆየት ነው" ብለዋል።
የአለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ድርጅት ሂውማን ራይትስ ዋች በፓኪስታን በታዳጊና በሴቶች ላይ የሚፈፀሙ ግድያዎች አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል ብሏል።
የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች "የክብር ግድያ" በሚባለው መንገድ በፓኪስታን አንድ ሺህ ሴቶች እንደተገደሉ ይናገራሉ።