የአቶ ለማ መገርሳ ድምጽ አየር ላይ እንዳይውል ተደርጓል ስለመባሉ ይጣራል ተባለ

የፎቶው ባለመብት, ኦሮሚያ ኮሚኒኬሽን ቢሮ
የኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትወርክ (ኦቢኤን) የቦርድ አባል እና የክልሉ ኮሚኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌታቸው ባልቻ፤ የአቶ ለማ መገርሳ ድምጽ በኦቢኤን እንዳይተላለፍ ስለመደረጉ የሚያውቁት ነገር እንደሌለና ስለጉዳዩ እንደሚጣራ ተናገሩ።
ኃላፊው አቶ ጌታቸው ለቢቢሲ እንደገለጹት የማንም ድምጽ በድርጅቱ እንዳይተላለፍ የተወሰነ ነገር እንደሌለ አመልክተው ተከስቷል ስለተባለው ጉዳይም መጣራት እንደለበት ተናግረዋል።
በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የሚተዳደረው የመገናኛ ብዙሃን ድርጅት የሆነው ኦቢኤን ላይ የክልሉ የቀድሞ ፕሬዝዳንትና የወቅቱ የአገሪቱ የመከላከያ ሚንስትር የሆኑትን የአቶ ለማ መገርሳ ድምጽ እንዳይተላላፍ ተደርጓል በሚል የድርጅቱ ጋዜጠኞች ቅሬታ ማሰማታቸውን መዘገባችን ይታወሳል።
ቢቢሲ ከድርጅቱ ጋዜጠኞች ባገኘው መረጃ መሰረት ረቡዕ እለት በአዳማ ከተማ በተፈጸመው የታዋቂው ባለሃብት በአቶ ከቢር ሁሴን ቀብር ላይ አቶ ለማ ተገኝተው ያደረጉት ንግግር 'ከላይ በመጣ ትዕዛዝ' በሚል በድርጅቱ ኃላፊዎች ድምጻቸው አየር ላይ እንዳይውል መደረጉ ተገልጿል።
ይህንንም ተከትሎ ቢቢሲ በጉዳዩ ላይ የድርጅቱ ዳይሬክተር ከሆኑት አቶ ዝናቡ አስራት እና ምክትላቸውን አቶ ቦጃ ገቢሳ ምላሽ ለማግኘት በስልክ ተደጋጋሚ ሙከራ ቢያደርግም የሁለቱም የእጅ ስልክ ባለመነሳቱ ሳይሳካ ቀርቷል።
ከዚህም በኋላ የኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትወርክ (ኦቢኤን) የቦርድ አባል እና የክልሉ ኮሚኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌታቸው ባልቻ "ይህ ሊሆን የሚችልበት ምንም መመዘኛ የለም" ሲሉ ለቢቢሲ የተናገሩ ሲሆን ጨምረውም "ይህ ጉዳይ መጣራት አለበት" ብለዋል።
ከዚህ ባሻገርም ስለክስተቱ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት የኦቢኤን ቦርድ ሰብሳቢ እና የኦሮሚያ ብልጽግና ፓርቲ ዋና ጸሐፊ አቶ አዲሱ አረጋን ለማግኘት ያደረግነው ጥረትም ሳይሳካ ቀርቷል።
አቶ ጌታቸው ከድርጅቱ እና ከቦርድ አባላት ጋር የዘወትር ሥራዎች እየተከናወኑ መሆን አስታውሰው፤ ይህ ጉዳይ ግን በቦርዱ ስብሰባ ላይ እስካሁን አለመነሳቱን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
"ሙያው በሚፈቅደው መሠረት አርትኦት ይሰራል እንጂ የዚህ ሰው ድምጽ ይተላለፍ' የዚህ ይከልከል የሚል ሰው የለም" ብለዋል።
የአቶ ለማ ድምጽ አየር ላይ እንዳይውል እንዴት ተከለከለ?
የአቶ ለማ ንግግርን የያዘው የቀብር ሥነ ሥርዓቱ ዘገባ ረቡዕ ዕለት ምሳ ሰዓት ላይ ስድስት እና ሰባት ሰዓት ላይ እንደሚሰራጭ በዕለቱ የጣቢያው መርሃ ግብር ላይ ተይዞ የነበረ ቢሆንም፤ ዜናው ወደ ምሽት እንዲተላለፍ መወሰኑን የድርጅቱ ሠራተኞች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ነገር ግን በዕለቱ ምሽት 12 እና 1 ሰዓት ዜናዎች ላይ ከዘገባው የአቶ ለማ መገርሳ ድምጽ እንዲወጣ ተደርጎ፤ የክልሉ የፕሬዝደንት አቶ ሽመልስ አብዲሳን ድምጽ በማካተት እንዲተላለፍ ተደርጓል።
አቶ ለማ በቀብር ሥነ ሥርዓቱ ላይ ያሉት ምን ነበር?
በታዋቂው ባለሃብት የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ ከተገኙት የክልሉና የፌደራል መንግሥቱ ባለስልጣናት አንዱ የነበሩት አቶ ለማ መገርሳ በቀብር ሥነ ሥርዓቱ ላይ ንግግር ለማድረግ ወደ መድረክ ሲያመሩ ለቀብር ከታደመው ሕዝብ ከፍ ባለ ጭብጨባ ነበር የተቀበላቸው።
የአቶ ለማ ንግግር ትኩረቱ የነበረው ሟቹ የንግድ ሰው በሁሉም ዘንድ ያላቸውን ታዋቂነትና ያበረከቱትን አስተዋጽኦ የሚዘክር እንደነበር በቀብር ሥነ ሥርዓቱ ላይ የታደሙ ሰዎች ለቢቢሲ ገልጸዋል።
አቶ ለማ ሟች ከቢር ሁሴንን እንደ አባትና ጓደኛቸው ይመለከቷቸው እንደነበር በማስታወስ "ትልቅ ትንሹ የሚያውቀው ሰው ነበረ። በንግድ ብቻ ሳይሆን ለወገኑ የሚጨነቅ ለኦሮሞ ብሎ ንብረቱን ያጣ ሰው ነው። ገንዘብ ቢኖረውም አንድም ቀን ለራሱ ጊዜ ያልነበረው ሰው ነበር። ኦሮሞ ዛሬ ትልቅ ሰው ነው ያጣው" የሚል ይዘት ያለው ንግግር ነበር ያደረጉት።












