የኦሮሚያ ክልል ቴሌቪዥን የአቶ ለማ መገርሳን ንግግር አላስተላልፍም ማለቱ እያወዛገበ ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የሚተዳደረው 'ኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትዎርክ' የክልሉ የቀድሞ ፕሬዝዳንትና የወቅቱ የአገሪቱ የመከላከያ ሚንስትር የሆኑትን የአቶ ለማ መገርሳ ድምጽ አላስተላልፍም ማለቱ በድርጅቱ ጋዜጠኞች ዘንድ ቅሬታን ፈጠረ።
ለረጅም ጊዜ ከአደባባይ ርቀው በመገናኛ ብዙሃን ሳይታዩ ቆይተው የነበሩት አቶ ለማ መገርሳ፤ ረቡዕ እለት አዳማ ውስጥ በተፈጸመው የታዋቂው ባለሃብት በአቶ ከቢር ሁሴን ቀብር ላይ ተገኝተው አጭር ንግግር አድርገው ነበር። ይህም የበርቶችን ትኩረት ስቦ ነበር።
በርካታ ባለስልጣናትና ታዋቂ ሰዎች የተገኙበትን የቀብር ሥነ ሥርዓት ለመዘገብ ከተገኙት መገናኛ ብዙሃን መካከል አንዱ የነበረው ኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትዎርክ (ኦቢኤን) በሥርዓተ ቀብሩ ላይ አቶ ለማ መገርሳ የተናገሩትን ድምጽ ከማስተላለፍ መቆጠቡ በድርጅቱ ጋዜጠኞች ዘንድ ጥያቄና ቅሬታን ፈጥሯል።
የአቶ ለማ ድምጽ አየር ላይ እንዳይውል እንዴት ተከለከለ?
የአቶ ለማ ንግግርን የያዘው የቀብር ሥነ ሥርዓቱ ዘገባ ረቡዕ ዕለት ምሳ ሰዓት ላይ ስድስት እና ሰባት ሰዓት ላይ እንደሚሰራጭ በዕለቱ የጣቢያው መርሃ ግብር ላይ ተይዞ የነበረ ቢሆንም፤ ዜናው ወደ ምሽት እንዲተላለፍ መወሰኑን የድርጅቱ ሠራተኞች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ነገር ግን በዕለቱ ምሽት 12 እና 1 ሰዓት ዜናዎች ላይ ከዘገባው የአቶ ለማ መገርሳ ድምጽ እንዲወጣ ተደርጎ፤ የክልሉ የፕሬዝደንት አቶ ሽመልስ አብዲሳን ድምጽ በማካተት እንዲተላለፍ ተደርጓል።
የመገናኛ ብዙሃን ድርጅቱ ዳይሬክተር አሉ እንደተባለው 'የአቶ ለማ ድምጽ ከላይ በመጣ ትዕዛዝ እንዳይተላለፍ ተከልክሏል' በሚል ምክንያት ድምጻቸው ከዘገባው ተቆርጦ እንዲወጣ መደረጉን ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ ሠራተኞች ተናግረዋል።
ይህ የዳይሬክተሩ ውሳኔ ከድርጅቱ ጋዜጠኞች ጋር አለመግባባትን ፈጥሮ እንደነበርም ቢቢሲ ያናገራቸው የኦቢኤን ጋዜጠኞች አረጋግጠዋል።
ከድርጅቱ ነባር ጋዜጠኞች መካከል አንዱ ለቢቢሲ፤ ከዚህ ቀደምም የተመረጡ ሰዎች ድምጽ እና ምስል አየር ላይ እንዳይውል ክልከላ ይደረጋል ሲል ይህ የመጀመሪያ ክስተት እንዳልሆነ ገልጿል።
የአቶ ለማ መገርሳ ድምጽ አይተላለፍም መባሉን ከተቃወሙ ጋዜጠኞች መካከል አንዱ የሆነው ጋዜጠኛ ደግሞ፤ "ይህ ሚዲያ የመንግሥት አፍ ብቻ ነበር። ድርጅቱ በሕዝቡ ዘንድ ድጋፍ እና ተደማጭነት እንዲያገኝ ብዙ ከሰሩት ሰዎች መካከል ዋናው አቶ ለማ መገርሳ ናቸው" በማለት፤ "እርሳቸው ያበረከቱት አስተዋጽኦ ዛሬ ላይ ተዘንግቶ፤ ድምጻቸው ሕዝብ ጋር እንዳይደርስ ማድረግ እጅግ ያበሳጫል" ሲል ተናግሯል።
ሌላው ማንነቱን እንዳይጠቀስ የጠየቀ ጋዜጠኛም "እኚህ ሰው በሕዝቡ ዘንድ ተቀባይነት ያላቸው ናቸው። የፖለቲካ ይዘት በሌለው ዘገባ ላይ ድምጻቸው አይተላለፍ ማለቱ ተቀባይነት የሌለው ነው" ሲል ቅሬታውን አሰምቷል።
የአቶ ለማ ድምጽ 'ከላይ በመጣ ትዕዛዝ አይተላለፍም' ከመባሉ ውጪ ለማን ድምጻቸው አየር ላይ እንዳይውል እንደተደረገ የተሰጠ ምንም አይነት ምክንያት እንዳልተሰጠ ጋዜጠኞቹ ተናግርዋል።
በጉዳዩ ላይ የድርጅቱ ዳይሬክተር የሆኑትን አቶ ዝናቡ አስራት እና ምክትላቸው አቶ ቦጃ ገቢሳ ጋር በስልክ በመደወል ማብራሪያና ምላሽ ለማግኘት ቢቢሲ ተደጋጋሚ ሙከራ ቢያደርግም ልናገኛቸው አልቻልንም።
አቶ ለማ በቀብር ሥነ ሥርዓቱ ላይ ያሉት ምን ነበር?
በታዋቂው ባለሃብት የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ ከተገኙት የክልሉና የፌደራል መንግሥቱ ባለስልጣናት አንዱ የነበሩት አቶ ለማ መገርሳ በቀብር ሥነ ሥርዓቱ ላይ ንግግር ለማድረግ ወደ መድረክ ሲያመሩ ለቀብር ከታደመው ሕዝብ ከፍ ባለ ጭብጨባ ነበር የተቀበላቸው።
የአቶ ለማ ንግግር ትኩረቱ የነበረው ሟቹ የንግድ ሰው በሁሉም ዘንድ ያላቸውን ታዋቂነትና ያበረከቱትን አስተዋጽኦ የሚዘክር እንደነበር በቀብር ሥነ ሥርዓቱ ላይ የታደሙ ሰዎች ለቢቢሲ ገልጸዋል።
አቶ ለማ ሟች ከቢው ሁሴንን እንደ አባትና ጓደኛቸው ይመለከቷቸው እንደነበር በማስታወስ "ትልቅ ትንሹ የሚያውቀው ሰው ነበረ። በንግድ ብቻ ሳይሆን ለወገኑ የሚጨነቅ ለኦሮሞ ብሎ ንብረቱን ያጣ ሰው ነው። ገንዘብ ቢኖረውም አንድም ቀን ለራሱ ጊዜ ያልነበረው ሰው ነበር። ኦሮሞ ዛሬ ትልቅ ሰው ነው ያጣው" የሚል ይዘት ያለው ንግግር ነበር ያደረጉት።
አቶ ከቢር ሁሴን ማናቸው?
አርሲ ውስጥ የተወለዱት አቶ ከቢር ሁሴን ታዋቂ የንግድ ሰው ነበሩ። በዘመናዊ ግብርና ሥራ ትልቅ ስም ያተረፉት አቶ ከቢር፤ አዳማ ከተማ ውስጥ የሚገኘው የአዳማ ጀነራል ሆስፒታል ባለቤትም ናቸው።
አቶ ከቢር የኦሮሞን ሕዝብ መሠረት በማድረግ የተመሰረቱ ባንኮች ስኬታማ እንዲሆኑ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማደረጋቸው ይነገራል።
ከዚህም በተጨማሪ በኦሮሞ የፖለቲካ ትግል ወቅት ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች እና ቤተሰቦቻቸውን ይረዱ እንደነበር የሚያውቋቸው ይናገራሉ።












