ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አል ሲሲን ተችቶ ለእስር የተዳረገው የፊልም ባለሙያ 'ሳኒታይዘር ጠጥቶ ህይወቱ አለፈ'
በሙዚቃ ቪዲዮ የግብጹን ፕሬዝደንት የተቸው የፊልም ባለሙያው ሻዲይ ሐባሽ በተመረዘ አልኮል ህይወቱ አለፈ ሲሉ የግብጽ ባለስልጣናት አስታወቁ።
የ24 ዓመቱ የፊልም ባለሙያ ካይሮ በሚገኘው እርስ ቤት፤ ከቀናት በፊት ውሃ መስሎት ሳኒታይዘር በመጠጣቱ ነው ህይወቱ ያለፈው ሲል አቃቤ ሕግ ተናግረዋል።
አቃቤ ሕጉ ጨምረውም የኮቪድ-19 ወረርሽኘን ለመከላከል ሳኒታይዘር በእስር ለሚገኙ ታራሚዎች ተከፋፍሏል ብለዋል።
የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ግን ለሻዲይ ሐባሽ ሞት ምክያቱ በቂ የህክምና ክትትል ማጣት ነው ሲሉ ይኮንናሉ።
ወጣቱ የፊልም ባለሙያ ፍርድ ቤት ሳይቀርብ ላለፉት ሁለት ዓመት በእስር ላይ የቆየ ሲሆን፤ "ሐሰተኛ ዜናዎችን ማሰራጨት" እና "የሕገ-ወጥ ድርጅት አባል መሆን" የሚሉ ክሶች ተመስርተውበት ነበር።
ሻዲይ ሐባሽ ለአስር የተዳረገው ከአገር ውጪ በስደት የሚገኘውን የራሚይ ኢሳም 'ባላህ' የተሰኘ ሙዚቃ ዳይሬክት [ካዘጋጀ] ካደረገ በኋላ ነበር። 'ባላህ' የሚለው ቃል በግብጽ ዝነኛ ፊልም ላይ ውሸታም ገጸ ባህሪን ወክሎ የሚተውንን ሰው ይወክላል። የፕሬዝደንት አል-ሲሲ ተቺዎችም ፕሬዝደንቱን 'ባላህ' ሲሉ ይጠሯቸዋል።
የዘፈኑን ግጥም የጻፈው ጋላል ኤል-ቤሃይሪ ከሁለት ዓመት በፊት የሶስት ዓመት እስራት ተፈርዶበታል።
ሻዲይ ሐባሽ ለሁለት ዓመታት በእስር ላይ ሲቆይ ለፍርድ አለመቀርቡ የፈጠረበትን ተስፋ ቢስነት በአንድ ደብዳቤ ላይ ገልጾ ነበር። ሻዲይ ሐባሽ "መቼ እና እንዴት እንደምወጣ ሳላውቅ በብቸኝነት ወደ አንደ ክፍል ከተወረወርኩ ሁለት ዓመታት አለፉ" ያለ ሲሆን ጨምሮም፤ "እስር አይደለም የሚገድለው፤ ብቸኝነት ነው" ብሎ ነበር።
ጠበቃ አህመድ አል-ካህዋጋ ለኤኤፍፒ ዜና ወኪል እንደተናገሩት፤ ኮቪድ-19 ወደ እስር ቤት እንዳይዛመት በማሰብ የግብጽ መንግሥት በማረሚያ ቤት ያሉ ሰዎች መጠየቅን መከልከሉን ተከትሎ በቅርቡ ሻዲይ ሐባሽን የጎበኘ ሰው የለም።
ጠበቃው እንዳሉት ሻዲይ ሐባሽ ወደ ሆስፒታል ተወስዶ ወደ ማረሚያ ቤቱ ከተመለሰ በኋላ ዓርብ ምሽት ህይወቱ አልፏል።
ማክሰኞ ዕለት አቃቢ ሕጉ በበኩላቸው ሐበሻ ወደ ሆስፒታል ባመራበት ወቅት ከመሞቱ አንድ ቀን በፊት ከፍተኛ መጠን ያለው እጅ ማጽጃ ሳኒታይዘር መጠጣቱን ተናግሯል ብሏል።
ሻዲይ ሐባሽ ሳኒታይዘሩን የጠጣው ከውሃ ጋር ተመሳስሎበት መሆኑን እና ከፍተኛ የሆድ ህመም ሲሰማው እንደነበረ ለሃኪሞች መናገሩን አቃቤ ሕጉ ጨምረው ተናግረዋል።
ይህን የሻዲይ ሐባሽን ሞት ምክንያት የሚጠራጠሩ በርካቶች ናቸው።
መንግሥት ለወጣቱ ፊልም ባለሙያ ሞት እንደምክንያት ያቀረበው ብዙ አጠራጣሪ ነገሮች አሉበት ይላሉ። ከፍተኛ ህመም ላይ ከነበረ ለምን በቂ ህክምና አልተደረገለትም፣ ሕግን በተጻረረ መልኩ ለምን ክስ ሳይመሰረትበት ለሁለት ዓመታት በእስር ላይ እንዲቆይ ተደረገ የሚሉ ጥያቄዎች ተነስተዋል።