ዶ/ር ቴድሮስ የሚመሩት ድርጅት ሥራው በትክክል ምንድነው? አገሮችንስ የማዘዝ ሥልጣን አለው?

ዶናልድ ትራምፕ የዓለም ጤና ድርጅትን ኮንነዋል። ሁለተኛ ገንዘብ አንሰጠውም ብለዋል። እንደ ትራምፕ አስተያየት ድርጅቱ አፍቃሪ-ቻይና ሆኗል፤ ኃላፊነቱንም በአግባቡ አልተወጣም።

ለመሆኑ የዓለም ጤና ድርጅት ኃላፊነት ምንድነው? አገራትን ይህን አድርጉ፣ ያን አታድርጉ ብሎ የማዘዝስ ሥልጣንስ አለው?

ማማከር እንጂ ማዘዝ አይችልም

ስዊዘርላንድ ከ50 በላይ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች አሉባት። ከነዚህ ውስጥ ሲሶው በጄኔቫ ነው የሚገኙት።

የዓለም ጤና ድርጅት ገና ወደ ቅጥር ሲገባ አረንጓዴና ማራኪ ነው። በየትኛው የግቢው ክፍል ማጨስ አይፈቀድም።

ወደ እንግዳ መቀበያው አዳራሽ ሲዘልቁ የሚያገኙት ብን ብን የሚሉ ባንዲራዎችን ነው፤ ለዓይን ይማርካሉ። ከኮርኒሱ ቁልቁል የሚወርዱት 194 ባንዲራዎች ንፋስ ያወዛውዛቸዋል። ከነዚህ መሀል የአሜሪካ ባንዲራ የመውረጃው ጊዜ ተቃርቦ ይሆናል።

ይህ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አካል የሆነው መሥሪያ ቤት የተመሰረተው በ1948 ነው። ራሱን "የዓለም ማኅበረሰብ የጤና ዘብ" ሲል ይጠራል።

ዋንኛ ግቡ የሰው ልጆች ሊያገኙት የሚገባውን የመጨረሻ የጤና ደረጃ እንዲያገኙት መትጋት ነው።

ትልቅ ኃላፊነት ይመስላል።

የ72 ዓመት የዕድሜ ባለጸጋ የሆነው የዓለም ጤና ድርጅት ባለፉት 11 ዓመታት ብቻ 6 ለዓለም ሥጋት የሆኑ ወረርሽኞችን በመቆጣጠር የተሳካ ሥራን ሠርቷል። ከነዚህ ውስጥ በምዕራብ አፍሪካ በ2014 የተቀሰቀሰው ኢቦላ፣ ከሁለት ዓመት በፊት የተነሳው ዚካ ቫይረስ እና አሁን ደግሞ በቻይና ዉሃን ከተማ የተነሳው ኮቪድ-19 ይጠቀሳሉ።

የዓለም ጤና ድርጅት፡-

  • ወረርሽኞች ሲቀሰቀሱ መቼ ለዓለም ጤና ሥጋት እንደሚሆኑ ያውጃል
  • የበሽታ ጥናት ያደርጋል፤ በሽታዎች መቼ የት እንደተቀሰቀሱ ይጠቁማል፣ ይከታተላል፣ አዳዲስ ክትባቶችና ሕክምናዎችን ያግዛል፣ ይደግፋል፣ ያረጋግጣል

በሽታዎች ወደተቀሰቀሱባቸው ሥፍራዎች ባለሞያዎችን ፈጥኖ ይልካል፤ መረጃ ይሰበስባል፤ ያጠናቅራል።

ከነዚህ ጥቅል የወል ተግባራቱ ባሻገር ድርጅቱ ፡-

  • ለስኳርና ያለቅጥ ውፍረት የሚዳርጉ ችግሮችን ለመቅረፍ ይሰራል
  • የትራፊክ አደጋን ለመቀስ ይሰራል
  • አንዳንድ ፖሊዮን የመሰሉ ክትባት የተገኘላቸው በሽታዎች ከዓለም ጨርሶ እንዲጠፉ ይከታተላል ይደግፋል
  • በወሊድ ወቅት ልጅም እናትም ለሞት እንዳይዳረጉ ይደግፋል፤ ወዘተ

ከዚህ በኋላ ነው ትልቁ ጥያቄ የሚነሳው።

ለመሆኑ የዓለም ጤና ድርጅት አገራትን የማስገደድ፣ መመሪያዎቹን እንዲፈጽሙ የማዘዝ ጉልበትና ሥልጣን አለውን? መልሱ የለውም ነው።

የዓለም ጤና ድርጅት ሥራው ማማከር ነው፤ ማገዝና መደገፍ ነው። ማዘዝ አይደለም።

ለአገሮች በጤና ዙርያ ሐሳብ አስተያየት ይሰጣል፤ አቅጣጫ ያስቀምጣል፤ የዜጎቻቸውን ጤና እንዲጠብቁ ያማክራል፣ አዳዲስ ወረርሽኞች እንዳይቀሰቀሱ ያበረታል፣ ይከላከላል መረጃ ያቀባብላል እንጂ በአገራት የጤና ጉዳይ ገብቶ ይህን ለምን አደረጋችሁ/አላደረጋችሁም ብሎ የመቅጣትም ሆነ የማዘዝ መብቱ የለውም።

የዓለም ጤና ድርጅት ኮቪድ-19 ላይ ተዘናግቶ ነበር?

መልሱ በመላሹ ማንነት ላይ ይወሰናል።

መላሹ ዶናልድ ትራምፕ ከሆኑ ድርጅቱ የሰነፍ ሥራ ነው የሠራው ይላሉ፡፡ ነገር ግን ዶናልድ ትራምፕ ራሳቸው በወረርሽኙ መባቻ ፈዘው ነበር፣ መፍዘዝ ብቻ ሳይሆን አፊዘው ነበር፣ ማፌዝ ብቻ ሳይሆን የአሜሪካዊያንን ሕይወት ለአደጋ አስጥተው ሰጥተዋል ተብለው እየተብጠለጠሉ ነው፡፡

እነሆ በእርሳቸው መፋዘዝ 600ሺ ዜጎች በተህዋሲው ተይዘዋል፤ 30ሺ ሞተዋል ይላሉ ተቺዎቻቸው፡፡

ዶናልድ ትራምፕ ዶ/ር ቴድሮስ የሚመሩትን ድርጅት በእንዝላልነትና በቻይና አፍቃሪነቱ ሲወነጅሉት ነበር፡፡

ጉዳዩን በቅርበት የተከታተሉ ጋዜጠኞችና ተንታኞች ግን ዶናልድ ትራምፕ ራሳቸው ቻይና ወረርሹን የተቆጣጠረችበት ፍጥነትና መንገድ አሞካሽተዋል፡፡ ይህም በትዊተር ሰሌዳቸው ዛሬም ድረስ አለ ይላሉ፡፡

ሆኖም ዶ/ር ቴድሮስ ቻይናን በማሞገሳቸው ዶናልድ ትራምፕ ዛሬም ድረስ የዓለም ጤና ድርጅትን ይወቅሳሉ፡፡ ይህ ብዙም ስሜት የሚሰጥ አይደለም፡፡

የዶናልድ ትራምፕ ከቻይና ጋር ያለባቸው ቁርሾ ፖለቲካዊ እንጂ ጤናዊ አይደለም ይላሉ፡፡

ይህን ካልን ዘንዳ የዓለም ጤና ድርጅት በኮቪድ-19 አያያዝ ጉዳይ ሲተች ትራምፕ የመጀመርያው አይደሉም፡፡

ለምሳሌ ወረርሽኙ ሲቀሰቀስ ጀምሮ መረጃ የነበራቸው የጤና ባለሞያዎችን ቻይና አፋቸውን እንዲይዙ ቅጣት ስትጥልባቸው ጭምር እንደነበር ይታወቃል፡፡ ይህ ብቻውን የዓለም ጤና ድርጅት ቻይናን እንዳያሞገስ ሊያደርገው አይገባም ነበር ወይ ሲሉ የሚጠይቁ አሉ፡፡

ቻይናዊያኑ የጤና ባለሞያዎቹ ስለ ወረርሽኙ የሰጡት ቅድመ ጥንቃቄ ቸል ተብሎ ሳለ እንዴት ቻይና በዓለም ጤና ድርጅት ሙገሳ ይገባታል?

የድርጅቱ አለቃ ዶ/ር ቴድሮስ አድኃኖም ገብረየሱስ ግን አሁንም በአቋማቸው እንደጸኑ ነው፤ በተደጋጋሚ ቻይና ወረርሽኙን ለመቆጣጠር ያደረገችው ፈጣን እርምጃ አድናቆት ይገባዋል ይላሉ፡፡

ምክንያቱም እንደ ዶ/ር ቴድሮስ አመለካከት ቻይና በሽታው ላይ ፈጣን እርምጃ በመወሰዷ ቀሪው ዓለም ለዝግጅት የሚሆን ጊዜን ገዝቷል፡፡

ዶ/ር ቴድሮስ ጨምረው እንደሚሉት ቻይና ከበጎ ፈቃድ ተነስታ ያለማቅማማት የተህዋሲውን ዘረመላዊ ቅንጣተ-ፍጥረት(ጄኔቲካል ኮድ) በፍጥነት ለዓለም አጋርታለች፤ ይህም አገራት ጊዜ ሳይወስዱ ክትባት የመፍጠርና ምርመራ የማድረግ ዕድል ፈጥሮላቸዋል፡፡

ታዲያ ይህን ሁሉ ያደረገችው ቻይና ብትደነቅ ምንድነው ክፋቱ?

ዶ/ር ዴቪ ሲዳሃር በኤደንበርግ ዩኒቨርስቲ የዓለም የኅብረተሰብ ጤና ፕሮፌሰር ናቸው፡፡ እርሳቸው በዶ/ር ቴድሮስ አረዳድ አይስማሙም፡፡

"ወረርሽኙ የመጀመርያ ምዕራፍ ላይ ቻይና ዘግይታለች፤ ቻይና ስኬታማ ሥራ ሰርታለች ለማለት እቸገራለሁ፤ መዘግየቶች ነበሩ፤ መጀመርያ አካባቢ እንዲያውም ነገሩን አቅለው ነበር ያዩት…" ይላሉ፡፡

ፕሮፌሰሯ በተለይ ድርጅቱ በምዕራብ አፍሪካ ለኢቦላ ወረርሽኝ ያሳየው ዳተኝነትን በተመለከተ አምርረው ሲተቹ የነበሩ ሴት ናቸው፡፡

"እርግጥ ነው ሁሉንም ችግሮች ድርጅቱ ላይ መደፍደፍ ይከብዳል፤ ምክንያቱም አገራት ሁሉ በእኩል ወረርሽኙ ለይ እንዲዘምቱ በማድረግና ሁሉንም በተመሳሳይ ደረጃ እንዲገኙ መጠበቅ ፈታኝ ነው፤ ሆኖም…"

የዓለም ጤና ድርጅት ሲታሰብ ትልቁ መዘንጋት የሌለበት ነጥብ ድርጅቱ የማዘዝ ሥልጣን የሌለው መሆኑ ነው፡፡ አብዛኛው ሥራው በአባል አገራት በጎ ፈቃድ የሚመሰረት ነው፡፡ ስኬቱም በዚያው መጠን በሌሎች መልካምነት የሚለካ ነው፡፡ አብዛኛው ሚናው የጤና ዲፕሎማሲ ነው ማለት ይቻላል፡፡

ለምሳሌ ዶ/ር ቴድሮስ የድርጅቱ አለቃ ስለሆኑ የቻይና መንግሥት ስለ ወረርሽኙ መረጃ እንዲያጋራ ሊያስገድዱት አይችሉም፡፡ አገራት ናቸው ወደ ድርጅቱ በፈቃዳቸው ቀርበው ሊያግዙ የሚችሉት፡፡

የኅብረተሰብ ጤና ፕሮፌሰሯ ዶ/ር ዴቪ የድርጅቱ ተቺ ቢሆኑም ዶ/ር ቴድሮስና ድርጅታቸው ያለባቸውን ውስንነት እንዲሁም አጣብቂኝ ፍንትው አድርጎ የሚገልጽ ነገር ተናግረዋል፡፡

" ዶ/ር ቴድሮስ (ትራምፕ እንደተመኙት) ቻይናን አምርረው ቢያወግዙ ኖሮ በደቂቃዎች የዓለም ጤና ድርጅት ዝናው ይናኝ ነበር፤ ሆኖም ያን ቢያደርጉ ኖሮ በኮቪድ-19 ዙርያ ለመከላከል የሚደረገውን ዓለም አቀፍ ጥረት ዜሮ ያስገባው ነበር"

ዶ/ር ዴቪ እንደምትለው ዶ/ር ቴድሮስ ቻይናዊያን በመጀመርያው የወረርሽኙ ምዕራፍ ስለ በሽታው የሚያውቁትን መረጃ እንዲያጋሩት ጠይቋቸዋል፤ ይህ ግን ከመጋረጃ ጀርባ የሆነ ነው የሚሆነው፡፡

"እኔ እንደሚገባኝ አንድን ነገር በይፋ በሚዲያ ፊት ማድረግና ነገሩን ከሚዲያ ጀርባ ማድረግ ልዩነት አለው፤ ለሚዲያ ፍጆታ አንድን ነገር ማድረግ ትወና ነው " ሲሉ ዶ/ር ቴድሮስ ከሚዲያ ጀርባ ጠንካራ ጥረት እንዳደረጉ ያላቸውን እምነት ይገልጻሉ፡፡

ድርጅቱ እንዲህ ሲብጠለጠል ዶ/ር ቴድሮስ የመጀመርያው ናቸው?

የዓለም ጤና ድርጅት መብጠልጠል የጀመረው በኮቪድ-19 አይደለም፡፡

በምዕራብ አፍሪካ ኢቦላ የተነሳ ጊዜ ከዚህ በባሰ ተተችቷል፡፡ ልዩነቱ ያን ጊዜ ተቺው ዶናልድ ትራምፕ ስላልነበሩ ብዙ ሚዲያ አላራገበው ይሆናል፡፡

የ2014ቱን የኢቦላ ወረርሽኝ የዓለም ቀውስ አድርጎ ለማወጅ ድርጅቱ 5 ወራት ወስዶበታል፡፡

በ2009 ደግሞ ድርጅቱ ስዋይን ፍሉን የዓለም ወረርሽን ብሎ ለማወጅ ተጣድፏል ሲባልም ይተቻል፡፡ ምናልባት ይህ ድርጅት አገራት የውስጥ ችግሮቻቸውን የሚያላክኩበት ተቋም ሆኖ ሳይታይ አይቀርም፡፡

በእርጋታቸውና ግርማ ሞገሳቸው የሚታወቁት ዶ/ር ቴድሮስ ትራምፕ ባሳለፍነው ሳምንት "ከእንግዲህ ገንዘብ ላንሰጣች እንችላለን" ሲሏቸው፤ "ነገሩን በፖለቲካ ባንለውስ ደስ ይለኛል" ሲሉ ጤናን ለፖለቲካ ፍጆታ እንዳያውሉት መክረዋቸው ነበር፡፡

ዶ/ር ቴድሮስ ጨምረውም ድርጅታቸው መተቸቱን በጸጋ እንደሚቀበሉት፤ ከስህታቸው እየተማሩ ጥንካሪያቸውን እያዳበሩ ወደፊት ብቻ እንደሚመለከቱ ተናግረው ነበር፡፡

ዶ/ር ቴድሮስ ያን ሳምንት ሐሳባቸውን ሲያሳርጉ "አሁን ቅድሚያ ማሰብ ያለብን ስለ ቫይረሱ ነው" ማለታቸው አይዘነጋም፡፡

የትራምፕ እርዳታ ጥንቅር ብሎ ቢቀርስ?

አሜሪካ ሁነኛዋ የድርጅቱ ደጋፊ ናት፡፡ ይህ አያጠያይቅም፡፡ የትኛውም አገር የአሜሪካንን ያህል ድርጅቱን በገንዘብ አይደግፍም፡፡ አገራት የሚያዋጡት ገንዘብ የሚወሰነው በበጎ ፈቃድ፣ በሕዝብ ብዛትና በሀብት መጠናቸው ነው፡፡

በበጎ ፈቃድ ወደ ድርጅቱ ካዝና የሚገባው የገንዘብ መጠን 2.2 ቢሊዮን ዶላር ከሚጠጋው የድርጅቱ አመታዊ በጀት ትልቁን ይይዛል፡፡

ባለፈው ዓመት ለምሳሌ አሜሪካ 400 ሚሊዮን ዶላር ነበር የሰጠችው፡፡

የእንግሊዝ ዌልካም ትረስት የተባለ በጎ አድራጎት ዳይሬክተር ዶ/ር ጄርሚ ፋራር "በዚህ ወቅት ድርጅቱ ገንዘብ የሚፈልግበት ጊዜ ነበር ብለዋል፡፡

"በዘመናቸውን ትልቁን የጤና ፈተና እየተጋፈጥን ነው፤ ይህን የሚያግዝ ሌላ ዓለም አቀፍ ድርጅት የለም፤ አብረን ማገዝ በሚገባን ጊዜ መከፋፈላችን ያሳዝናል" ብለዋል ዶ/ር ጄርሚ፡፡

ፕሮፌሰር ዴቪ የአሜሪካ ገንዘብ አላዋጣም ማለት ኮቪድ-19 ብቻም ሳይሆን ወባን፣ፖሊዮን እና ሌሎች በርካታ በሽታዎችን በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዳንዋጋ የሚያደርግ ነው፡፡