ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኮሮናቫይረስ- የዓለም መሪዎች በማህበራዊ ሚዲያ ያጋሩት መረጃ ሐሰተኛ በሚል እየተሰረዘ ነው
ፌስቡክና ትዊተር የዓለማችን መሪዎችን በማህበራዊ ሚዲያዎቻቸው ላይ ያጋሩትን ምስልና ጽሑፍ ስለኮሮናቫይረስ ሐሰተኛ መረጃ ይዟል በሚል እያጠፉት ይገኛሉ።
ፌስቡክ የብራዚሉን ፕሬዝዳንት፣ ቦልሶናሮ ያጋሩትን ተንቀሳቃሽ ምስል ሐሰተኛ መረጃ ይዟል በሚል ሰርዞባቸዋል። ፕሬዝዳንቱ ሃይድሮክሲክሎሮክዊን የተሰኘው መድሃኒት ቫይረሱን ያድናል የሚል መልዕክት ነበር በፌስ ቡክ ያጋሩት።
ፕሬዝዳንቱ በተደጋጋሚ ስለኮሮናቫይረስ ያላቸው አመለካከት ዝቅ ያለ መሆኑን ያሳዩ ሲሆን፣ ሰዎች በቫይረሱ ቢያዙም ሕክምና ድጋፍ እንዳይፈልጉ እንዲሁም አካላዊ ርቀትን መጠበቅ እንደማይገባ ሲገልፁ ተደምጠዋል።
የቬንዙዌላው ፕሬዝዳንት ደግሞ ቤት ውስጥ የተቀመመ የፈውስ መድሃኒትን በትዊተር ገፃቸው ላይ አጋርተው የነበረ ሲሆን ትዊተርም ይህንኑ አጥፍቷል።
ሁለቱም የማህበራዊ ሚዲያዎች ከዚህ ቀደም መሪዎች የሚያሰራጯቸውን መልዕክቶች ብዙም ለመሰረዝ አይደፍሩም ነበር።
ትዊተር ከዚህ ቀደም የዓለም መሪዎችን መልዕክት "የሕዝብ ፍላጎትን" በመጥቀስ አይሰርዝም ነበር። ነገር ግን በአሁኑ ሰዓት ከቫይረሱ እኩል እየተሰራጨ ያለውን የሐሰተኛ መረጃ ለመግታት ማህበራዊ ሚዲያዎቹ ጫና በዝቶባቸዋል።
ትዊተር የሕክምና መረጃ መመሪያውን ያሻሻለ ሲሆን ከዓለም አቀፉ የማህበረሰብ ጤና መመሪያ ጋር እንዲጣጣም አድርጎታል።
ፌስቡክም አካላዊ ጉዳት የሚያደርሱ መረጃዎችን ለማጥፋት ተግቶ እየሰራ ነው።
የብራዚሉ ፕሬዝዳንት፣ ቦልሶናሮ በማህበራዊ ሚዲያዎቻቸው ላይ ያጋሩት ተንቀሳቃሽ ምሰል በታጉአቲንጋ ጎዳናዎች ላይ ሲያዋሩ የተቀረፀ ነበር።
ፌስቡክ ተንቀሳቃሽ ምስሉን የሰረዝኩት የማህበረሰብ ደህንነት ፖሊሲዬን ስለሚቃረን ነው ሲል ለቢቢሲ ቢገልጽም በኋላ ግን መረዳት እንደተቻለው ፕሬዝዳንቱ ስለ 'ሃይድሮክሲክሎሮክዊን' መድሃኒት ፈዋሽነት በመናገራቸው መሆኑ ታውቋል።
ፌስቡክ ምስሉን ከሚያስተዳድረው ኢንስታግራምም ጭምር ማውረዱን ለመረዳት ተችሏል።
የዓለም ጤና ድርጅት የተለያዩ መድሃኒቶች በአንድ ላይ ሊሰጡ እንደሚችሉ ነገር ግን እስካሁን ድረስ ኮሮናን የሚፈውስ የተረጋገጠ መድሃኒት አለመኖሩን አስታውቋል።
ሃይድሮክሲክሎሮክዊን እንዲሁም ክሎሮክዊን ለኮቪድ-19 ፈዋሽነታቸው ያልተረጋገጠ በሙከራ ላይ ያሉ መድሃኒቶች ናቸው።
በርግጥ ክሊኒካል ፍተሻ ባያልፉም የአሜሪካው ምግብና መድሃኒት አስተዳደር ሁለቱን በፀረ ወባ መድሃኒትነት የሚታወቁትን መድሃኒቶች፣ "ለአስቸኳይ ጊዜ ጥቅም" በማለት በኮሮና ታምመው ወደ ሆስፒታል ለመጡ ሕሙማን እንዲሰጡ ፈቅዷል።
ነገር ግን ባለፈው ሳምንት የአሜሪካ ምግብና መድሃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን ከማረጋገጡ በፊት ፕሬዝዳንት ትራምፕ እነዚህ መድሃኒቶችን ፈዋሽ ናቸው ሲሉ ተናግረው ነበር።
እንዲሁም የፕሬዝዳንቱ የግል ጠበቃ መድሃኒቱ "መቶ በመቶ ፈዋሽ ነው" በማለታቸው የትዊተር መልዕክታቸው ተሰርዟል።