ሶማሊያ በዓለም አቀፍ አበዳሪዎች ከፍተኛ የብድር ስረዛ ተደረገላት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የዓለም ባንክና ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ሶማሊያ ብድር እንዲቃለልላት የሚያስችሉ እርምጃዎችን መውሰዷን ማስታወቃቸውን ተከትሎ የአበዳሪዎችን ድጋፍ አግኝታለች።
እንደ መግለጫው ከሆነ ሶማሊያ አጠቃላይ ብድሯ ከ5.2 ቢሊዮን ዶላር በከፍተኛ ደረጃ ዝቅ ይደረግላታል። ይህም የሚሆነው በሦስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ነው።
በሶማሊያ የዓለም ባንክ ተወካይ ሁግ ራይደል ለቢቢሲ እንደገለጹት የሶማሊያን የብድር መጠን ለማቃለል ከሚወሰደው የተቀናጀና ሰፊ ሂደት መካከል ይህ የመጀመሪያው እርምጃ ነው ብለዋል።
ሶማሊያ ከ30 ዓመት በፊት ከነበረው የእርስ በርስ ጦርነት ጀምሮ ብድሯን ከፍላ አታውቅም፤ በዚህ ምክንያትም ሶማሊያ ከተለያዩ አበዳሪ ተቋማት እንደገና ብድር ለማግኘት የምታደርገውን ጥረት ከባድ አድርጎባታል።
አሁን ግን ይህ የብድር ስረዛ ስለተደረገላት መንግሥት በመላ አገሪቱ ለሚያከናውናቸው አገልግሎቶች ብድር ለመጠየቅ ያስችለዋል።
የሶማሊያው ጠቅላይ ሚንስትር ሃሰን አሊ ጉዳዩን አስመልክተው በሰጡት አስተያየት "ይህ ከነጻነት በኋላ ያገኘነው ሁለተኛው ነጻነት ነው" ብለዋል፤ ከቅኝ ግዛት ነጻ የወጡበትን ሁኔታ በማጣቀስ።
"አሁን ያለንበት ጊዜ በጣም አስቸጋሪ ሁኔታ በመሆኑ በአበዳሪ ተቋማቱ በተወሰደው እርምጃ መሰረት ልናገኘው የምንችለው የበጀት ድጋፍ በመላ አገራችን ለሕዝቡ አገልግሎት ለመስጠት ትልቅ እገዛ ያደርጋል። ከሁሉም በላይ ደግሞ ሁላችንንም እያሸበረን ያለውን ኮሮናቫይረስን ለመዋጋት ይረዳናል" ብለዋል ጠቅላይ ሚንስትሩ።
እንደ ሶማሊያ ባለ በሽብርተኞች በተደጋጋሚ ጥቃት ለሚደርስበት አገርም ሽብርተኝነትን ማሸነፍ የሚቻለው ምጣኔ ሃብትን በማሳደግ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚንስትሩ ወጣቶችንና ሴቶችን የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።
አክለውም ፍትሃዊና ግልጽ የሃብት ክፍፍል በመፍጠር ሽብርተኝነትን ማሸነፍ ስለሚቻል የብድር ቅነሳ ውሳኔው ለሶማሊያ ዘርፈ ብዙ ጥቅም የሚያመጣ መሆኑን ጠቅላይ ሚንስትር ሃሰን ተናግረዋል።













