የዓለማችን የደስተኞች አገር ዜጎች የደስታቸው ምንጭ ምንድን ነው?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ምንም እንኳን በተለያዩ ጊዜያት የተፈጥሮ አደጋዎች ቢደጋግሟትም በፓሲፊክ ውቂያኖስ ላይ የሚገኙ ደሴቶች ስብስብ የሆነችው አገር በዓለማችን እጅግ ደስተኛ ዜጎች የሚኖሩባት እንደሆነች ታውቋል።
ቫኑዋቱ የሀገሪቱ ስም ሲሆን በፓሲፊክ ውቂያኖስ መሀል ላይ ነው የምትገኘው። ከአውስትራሊያ በ2000 ኪሎሜትር ርቅት ላይ የሚገኙት ደሴቶች ብዛታቸው ከ80 በላይ ነው።
'ሃፒ ፕላኔት ኢንዴክስ' የተባለው ሪፖርት የዓለማችንን ደስተኛ አገራት ደረጃ ያስቀምጣል። በዚህም መሰረት በጣም ደስተኛ ናቸው ከተባሉት አራት አገራት መካከል ቫኑዋቱ መካተት ችላለች።
ደረጃው የሚወጣው የአገሪቱን ደህንነት፣ የእድሜ ጣሪያ፣ የእኩልነት ደረጃ እንዲሁም በርካታ ተፈጥሯዊ ሀብቶችን ከግምት ውስጥ በማስገባት ነው ተብሏል።
ለመሆኑ ይህችን ትንሽ አገር ደስተኛ ያደረጋት ምንድነው?
ቫኑዋቱ እ.አ.አ. በ 1980 ከእንግሊዝና ፈረንሳይ ጥምር ቅኝ ግዛት ነጻነቷን ካገኘች በኋላ ማንኛውንም የአገሪቱ ክፍል ለማንኛውም ግለሰብም ሆነ አገር መሸጥ ክልክል ሆኗል። የደሴቶቹም ብቸና ባለቤቶች ለቫኑዋቱ ነባር ህዝቦች መሆኑ ታውጇል።
በአውሮፓውያኑ 2011 ዓ.ም የቫኑዋቱ ስታቲስቲክስ ቢሮ ያወጣው መረጃ በደሴቶቹ መሬት ያላቸው ዜጎች ከሌላቸው ጋር ሲነጻጸር የበለጠ ደስተኛ መሆናቸውን ያሳያል።
በአሁኑ ጊዜ አገሪቱ ካላት 280 ሺ ዜጋ መካከል ሦስት አራተኛ የሚሆኑት በገጠራማ ክፍሎች ውስጥ የሚኖሩ ሲሆን ሁሉም በሚባል መልኩ የራሳቸው የእርሻ መሬት አላቸው። አብዛኛዎቹም የሚበሉትን ምግብ ከማሳቸው ያገኛሉ።

የፎቶው ባለመብት, AFP
ከዚህ በተጨማሪ እንደ አሳማ፣ ኮኮናት እና ጭንቀትንና ህመምን ለማስታገስ የሚጠቅመው 'ካቫ' የተባለው ተክል በደሴቲቱ በቀላሉ ማግኘት የሚቻሉና አብዛኛውን ጊዜ ያለምንም ክፍያ ሰዎች የሚለዋወጧቸው ነገሮች ናቸው።
ሌላኛው ለደስተኝነታቸው ምንጭ ነው ተብሎ የተቀመጠው ነገር ዜጎች ከቀደመው ባህላቸውና እሴቶቻቸው ጋር ያላቸው የጠበቀ ቁርኝት ነው። ከቤተሰብ አመሰራረት እስከ ልጅ አስተዳደግ፣ ከምግብ አሰራር እስከ የዕለት ተዕለት ግንኙነታቸው ድረስ ሁሉም ነገር ከባህልና እሴቶቻቸው ጋር የተቆራኙ ናቸው።
ቫኑዋቱ ከ80 በላይ ደሴቶች የተወጣጣች እንደመሆኗ በርካታ ተፈጥሯዊ ሀብቶች አሏት። እጅን አፍ ላይ የሚያስጭኑ ናቸው የሚባልላቸው የቫኑዋቱ ደሴቶች ለሀገሬው ዜጎች የእለት ተዕለት መዝናኛዎች ናቸው።
ቫኑዋቱ 'ምድራችን ለዘላለም' እንደ ማለት ሲሆን በደሴቶቹ የሚኖሩት ህዝቦች 139 ቋንቋዎችን ይናገራሉ። ይህ ደግሞ እጅግ በርካታ ቋንቋዎች ከሚነገርባቸው የዓለማችን አገራት መካከል አንዷ ያደረግታል።
92 በመቶ የሚሆነው የቫኑዋቱ ዜጋ አገር በቀል ቋንቋዎችን በደንብ መናገር ይችላል። በተጨማሪም አብዛኛው የአገሬው ዜጋ ተክሎች መቼ መተከል እንዳለባቸው፣ መቼ መሰብሰብ እንዳለባቸው፣ የቤተሰብ ታሪክ እና የተፈጥሮ እንክብካቤ እውቀታቸው ከፍተኛ ነው።
የቫኑዋቱ ዜጎች እነዚህና ሌሎች በርካታ ያልተጠቀሱ ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ ሀብቶች ምክንያት ደስተኛ ቢሆኑም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን እንደ የባህር ጠለል ከፍ ማለት ያሉ የተፈጥሮ አደጋዎች ስጋት ሆነውባቸዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ዩኒቨርሲቲ በ2014 ባወጣው ሪፖርት መሰረት የቫኑዋቱ ደሴቶች ለተፈጥሯዊ አደጋዎች እጅግ የተጋለጡ እንደሆነ ገልጿል።













