ትሬቨር ኖዋ ከቢል ጌትስ ጋር በቴኒስ ጨዋታ ሊፋለም ነው

የፎቶው ባለመብት, John Lamparski
የተወዳጁ 'ዘ-ዴይሊ ሾው' አዘጋጅ እውቁ ደቡብ አፍሪካዊ ቀልደኛ ትሬቨር ኖዋ ከአሜሪካዊው ቢሊየነር ቢል ጌትስ ጋር በቴኒስ ጨዋታ እንደሚፋለሙ በትዊተር ገፁ ይፋ አድርጓል።
በዚህ ጨዋታ ሁለቱም ግለሰቦች ከስመ ጥር የቴኒስ ተጫዋቾች ጋር የሚጣመሩ ሲሆን ትሬቨር ከራፋኤል ናዳር ጋር እንዲሁም ቢል ጌትስ ከሮጀር ፌደረር ጋር በመሆን የቡድን ፍልሚያቸውን ያደርጋሉ።
ጨዋታቸውም በሚቀጥለው ሳምንት በደቡብ አፍሪካዋ ከተማ ኬፕታውን ሊካሄድ ቀነ ቀጠሮ ተይዞለታል።
ይህ ጨዋታ በታዋቂው የቴኒስ ተጫዋች ሮጀር ፌደረር ስም ለተሰየመው ፋውንዴሽን ገንዘብ ለማሰባሰብ በአፍሪካ ውስጥ የሚደረገው ዘመቻ አካልም ነው ተብሏል።
ድርጅቱ እንዳሳወቀው ገንዘቡ በድህነት የሚኖሩ ልጆችን የወደፊት ህይወታቸውን የሚቀይሩበትን መንገድ ያመቻቻል።
ነዋሪነቱን በአሜሪካ ያደረገው ቀልደኛው ከዓለማችን ኮሜዲያን አራተኛው ከፍተኛ ተከፋይ በመሆን በዘንድሮው ዓመት የፎርብስ የዓለማችን ቱጃሮች ዝርዝር ውስጥ ስሙ ሰፍሯል።
በደቡብ አፍሪካዋ ሶዌቶ የተወለደው ትሬቨር፤ በመፅሔቱ ዝርዝር ውስጥ እስከ አስር ባሉት ደረጃዎች ውስጥ ሲሰፍር ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።
የ35 ዓመቱ ትሬቨር ባለፈው ዓመት ብቻ በ 'ዘ ዴይሊ ሾው' የሚያዘጋጀው የቴሌቪዥን ፕሮግራምን ጨምሮ ከተለያዩ ፕሮጀክቶች 28 ሚሊየን ዶላር ገቢ አግኝቷል።
ይሁን እንጂ ሀብቱ እያደገ የመጣው በዓለም አገራት ካካሄዳቸው 70 የሥራ ጉዞዎች ሲሆን ይህም ገቢው በቱጃር 'ስታንድ አፕ ኮሜዲያን' ዝርዝር አራተኛውን ደረጃ እንዲይዝ አስችሎታል።












