በተቀመጠው የጊዜ ገደብ በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ከስምምነት ሳይደረስ ቀረ

በህዳሴ ግድብ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በኢትየጵያ፣ በሱዳንና በግብጽ መካከል በህዳሴ ግድብ ዙሪያ ያለውን አለመግባባት ለመፍታት ሲካሄድ የነበረው ውይይት ከምን ላይ እንደደረሰ ከተሳታፊዎቹ አልተሰማም።

የሶስቱ አገራት የውጪ ጉዳይ እና የውሃ ሚንስትሮች በዋሽንግተን ዲሲ ተገናኝተው የመከሩ ሲሆን፤ ቀድሞ በተቀመጠው የጊዜ ገደብ መሠረት ሦስቱ አገራት የደረሱትን ስምምነት ትናንት ይፋ እንደሚያደርጉ ተጠብቆ ነበር።

ከሁለት ሳምንታት በፊት ሦስቱ አገራት እንዲሁም አሜሪካ እና የዓለም ባንክ በጋራ ባወጡት መግለጫ ላይ በሕዳሴው ግድብ ሙሊት እና ሌሎች መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ከስምምነት በሚያደርሱ ነጥቦች ላይ ተግባብተናል ብለው ነበር።

በአፍሪካ ግዙፉ የኤሌክትሪክ ማመንጫ ግድብ እንደሆነ በተነገረለት የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ውሃ አሞላል ዙሪያ የተፈጠረውን ልዩነት ለማጥበብ በተከታታይ ዋሽንግተንን ጨምሮ በሦስቱ አገራት መዲናዎች ሲካሄድ ቆይቷል።

የሦስቱ አገራት የውጪ ጉዳይና የውሃ ሚኒስትሮች ግድቡ ውሃ የሚሞላበትን እና ሥራ የሚያከናውነትን ሁኔታ ላይ የመጨረሻ ስምምነት ላይ ለመድረስ ባለፉት ሁለት ቀናት ዋሽንግተን ዲሲ ውስጥ ውይይት ሲያደርጉ ቆይተዋል።

በአሜሪካ የገንዘብ ሚኒስቴርና በዓለም ባንክ በታዛቢነት በተገኙበት የቀረበው ረቂቅ የስምምነት ሰነድ እንደሚያመለክተው በአባይ ወንዝ ላይ እየተገነባ ያለው ግድብ በዝናብ ወቅት በተለያዩ ደረጃዎች በውሃ እንዲሞላ የሚመክር ነው።

ነገር ግን የውሃ ሙሌቱ በምን ያህል ጊዜ ውስጥ እንደሚከናወን አይጠቅስም፤ ይህም አገራቱ በሚያደርጉት ውይይት ዝርዝሩ ሂደት በመጨረሻው ስምምነት ላይ ይደርሳል ተብሎ ነበር።

የግድቡ ውሃ አሞላል በተመለከተ ያለው ጉዳይ ለረጅም ጊዜ አጨቃቂ ሆኖ ቆይቷል።

ኢትዮጵያ የግድቡን ግንባታ ለሚያስፈልጋት የኃይል አቅርቦት በጣም ወሳኝ እንደሆነና ለዚህም ግድቡ በተቻለ ፍጥነት የውሃ ሙሌቱ በቶሎ እንዲጀምር ፍላጎት አላት።

ዘጠና በመቶ የሚሆነውን የውሃ ፍላጎቷን ከአባይ የምታገኘው ግብጽ ግን ግድቡ በፍጥነት የሚሞላ ከሆነ የምታገኘው የውሃ አቅርቦቷን ሊጎዳው እንደሚችል ስጋቷን እየገለጸች ነው።

ከዓመታት በፊት ግንባታው ለተጀመረውና 4 ቢሊዮን ዶላር ወጪን ለሚጠይቀው በአባይ ወንዝ ላይ ለሚገነባው ግድብ፤ ኢትዮጵያ 85 በመቶ የሚደርሰውን ውሃ የምታበረክት ሲሆን፤ ግድቡ በስድስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ በውሃ እንዲሞላ ፍላጎት አላት።

ግብጽ ግን ከአባይ ወንዝ የምታገኘው የውሃ መጠን በከፍተኛ ሁኔታ እንዳይቀንስባት የውሃ ሙሌቱ ከ10 እስከ 20 ዓመታት በሚደርስ ጊዜ ውስጥ እንዲሞላ ትፈልጋለች።