የኃይማኖት መፃዒ ዕጣ ፈንታ ምን ይሆን?

የኃይማኖት ዕጣ ፈንታ ምን ይሆን?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ከሞሐመድ በፊት፤ ከክርስቶስ ቀድሞ፤ ከቡድሃም ቀድሞ ዞራስተር ነበረ። ከ3500 ዓመት በፊት፤ በነሃስ ዘመን ኢራን የአንድ አምላክን ርዕይ ይዞ የተነሳ።

ከ1000 ዓመት በኋላ በዓለማችን የአንድ አምላክን ሥርዓት በማስረፅ የመጀመሪያ የሚባልለት ዞራስተር በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተከታዮችን ማፍራት ቻለ። አብዛኛዎች የፋርስ ባሕረ-ሰላጤ ነዋሪዎች ናቸው።

ከ1000 ዓመት በኋላ ግን የፋርስ አገዛዝ ፈረሰ፤ ዞራስተሮችም አናሳ ሆኑ፤ እያሳደደ የሚገድላቸውም በዛ። ይህን አድራጊው ደግሞ አዲሱ የፋርስ ባሕረ-ሰላጤ ኃይማኖት ነው. . . እስልምና።

ከ1500 ዓመታት በኋላ አሁን ባለንበት ዓለም የዞራስተር ተከታዮች ቁጥራቸው እጅግ የመነመነ ነው። እየሞተ ያለ ኃይማኖት እየተባለ ይጠራም ይዟል።

ኃይማኖት ይወለዳል፤ ያድጋል፤ ከዚያም ይሞታል ተብሎ ቢታሰብም ማንም ይህንን መቀበል የሚፈልግ አይመስልም። አዲስ ኃይማኖት የሚመሠርቱ ሰዎች ይወገዛሉ እንጂ አይሞገሱም።

በርካቶቻችን ኃይማኖትን እንደ ጊዜ እና ቦታ የማይገድበው አድርገን እንቆጥረዋለን። ኃይማኖት ሲሞት ተረት ይሆናል። ልክ እንደ ግብፅ፣ ግሪክ እና ኖርስ አማልክት።

ዛሬ ኃያል የምንላቸው ኃይማኖቶች በዝግመተ ለውጥ ያለፉ ናቸው። ለምሳሌ ክርስትና አነስ ባለች ቤተ-እምነት እንደ ተጀመረ መዛግብት ይጠቁማሉ። ክርስትና ከሶስት ክፍለ ዘመናት በኋላ በደንቡ እውቅና ማግኘት የቻለው። ከዚያ በኋላ ነው ክርስትና ምስራቃዊ ኦርቶዶክስ እና ካቶሊክ ተብሎ ለሁለት የተከፈለው [ከክርስቶስ ልደት በኋላ በ1054 ዓ.ም።]

እርስዎ የሚያምኑበት ኃይማኖት የእውነት ጫፍ ላይ ደርሷል ብለው ካመኑ ሊቀየር ይችላል ብለው የሚያስቡበት ምንም ምክንያት የለም። ነገር ግን ታሪክ የሚነግረን ሌላ ነው። ኃይማኖቶች እንደ ትውልዱ ይቀያየራሉ፤ ሊጠፉም ይችላሉ።

ኃይማኖቶች ባለፉት ክፍለ-ዘመናት ብዙ ለውጥ እንዳሳዩ ከመዛግብት ከተረዳን ዘንዳ መጪው ዘመን ምን አዝሏል የሚለውን መጠየቅ ግድ ነው። በአንድ አምላክ ማመን እየጠፋ ይመጣ ይሆን? ቴክኖሎጂስ ምንም ዓይነት ተፅዕኖ ይኖረዋል? አዲስ መልክ ያለው ኃይማኖት ብቅ ይል ይሆን?

የኃይማኖት መፃዒ ዕጣ ፈንታ ምን ይሆን?

የፎቶው ባለመብት, Amir Levy

የኃይማኖት አስፈላጊነት. . .

የ18ኛው ክፍለ ዘመን ፈረንሳዊ ባለቅኔ ቮልቴር «ፈጣሪ ባይኖር እንኳ፤ ልንፈጥረው ግድ ነው» ሲል ተደምጦ ነበር። እርግጥ ቮልቴር የተደራጀ ኃይማኖት ቀንደኛ ነቃፊ ነበር። ቢሆንም ፈጣሪ አለ ብሎ ማመን ለማሕበረሰቡ አስፈላጊ ነው ብሎ ያምናል።

ዘመናይ ነን የሚሉ የኃይማኖት አጥኚዎችም በዚህ ያምናሉ። ኃይማኖት የሰፊው ሕዝብ ማደንዘዣ ዕፅ ነው የሚለው እሳቤም የመጣው ከዚህ ነው። ኃይማኖት አስፈላጊነቱ ባይከራክርም ይላሉ ፀሐፊያኑ፤ ባለሥልጣናት ሕዝቡን ለመግዛት ሊጠቀሙበት አይገባም።

በርካታ ኃይማኖቶች በየጊዜው ይፈጠራሉ። ነገር ግን መዝለቅ አይችሉም። አሁን በርካታ ተከታይ ያላቸው ኃይማኖቶችም አንድ ሰሞን እንዲሁ ነበሩ። የኃይማኖቶች ዕጣ ፈንታ የሚወሰኑ ለምዕመኑ በሚያቀርቡት ጥቅም ላይ ነው።

ለምሳሌ ክርስትና በሮም ሥልጣኔ ወቅት አንድ ተራ ቤተ-እምነት እንደነበር አጥኚ ኮነር ዉድ ይናገራሉ። ነገር ግን በሽታ መጥቶ የሮም ሰዎችን ሲያጠቃ የክርስትና እምነት ተከታዮች እርስ በርስ ተረዳድተው ሲተርፉ ኢ-አማንያን ግን አለቁ። እስልምናም ቢሆን ለክብር እና መረዳዳት የሚሰጠው ቦታ በውቅቱ ለነበሩ ኢ-አማንያን አዲስ ነገር ነበር።

ወጣም ወረደ ኃይማኖት ለማሕበረሰብ ከሚሰጣቸው በርካታ ጥቅሞች መካከል አንዱ ሰዎች እርስ በርስ ተቻችለው እንዲኖሩ ማድረጉ ትልቁ እንደሆነ ብዙዎች ይስማማሉ።

ነገር ግን ኃይማኖት የለንም የሚሉ ሰዎች ቁጥር እጅጉን እየበዛ መጥቷል። አሊያም በኃይማኖታቸው አገዛዝ ሥር ለመውደቅ ብዙም የማይሹ የትየለሌ ናቸው። ኃይማኖትና መንግሥታዊ አገዛዝም እየተራራቁ ናቸው። ሰዎች ለፈጣሪ ሕግ ከመገዛት ይልቅ ለመንግሥታዊ ሕግ መገዛት እየቀናቸው ነው። ይህ ሁሉ ተደማምሮ የኃይማኖት ዕጣ ፈንታ አሳሳቢ ነው ማለት አያስገርምም።

እንደ ቻይና እና ሩስያ ያሉ ኮሚኒስት ሃገራት ፈጣሪ የለም የሚለውን ሃሳብ [ኤቴይዝም] እንደ ሃገራዊ ፖሊሲ አፅድቀዋል። በተለይ ቻይና ውስጥ እምነትን ማንፀባረቅ ቀላል አይደለም።

ኃይማኖት አልባ ሰዎች የሚገኙት ደግሞ በለፀጉ በሚባሉ ሃገራት ነው። ለምሳሌ ጃፓን እና ስዊድን በርካታ ኃይማኖት የለሽ ሰዎች የሚገኙባቸው ሃገራት ናቸው። በጣም የሚያስደንቀው ግን በላቲን አሜሪካና በአረቡ ዓለም በርካታ ቁጥር ያለው ኃይማኖት የለሽ ሰው መገኘቱ ነው።

ሌላው ቀርቶ የኃይማኖት [በተለይ ደግሞ ክርስትና] ተፅዕኖ ጎልቶ በሚታይባት ሃገረ-አሜሪካ ኃይማኖት የለንም የሚሉ ሰዎች ቁጥር ከኢቫንጀሊካል ክርስቲያኖች ቁጥር እየላቀ መምጣቱን የአሜሪካ አጠቃላይ የማሕበረሰብ ጥናት [General Social Survey of US] ይፋ አድርጓል።

ቢሆንም ኃይማኖት እየጠፋ ነው ለማለት ፈፅሞ አያስደፍርም። በግሪጎሪ አቆጣጠር 2015 ላይ 'ፒው ሪሰርች' የተሰኘው ያሠራው ጥናት የአማኞች ቁጥር እየጨመረ እንጂ እየቀነሰ እንማይሄደ ያሳያል። የእስልምና እምነት ተከታዮች ቁጥር እየጨመረ ከክርስትያኖች እኩል ሊሆን እንደሚችልም ጥናቱ ይገምታል።