ሱዳን በእስር ቤት የነበረን መምህር ገድለዋል በተባሉት ላይ የሞት ፍርድ አስተላለፈች

የሱዳን ፍርድ ቤት አንድ አስተማሪን በእስር ላይ ሳለ አሰቃይተው ለሞት ዳርገውታል በሚል በ29 የደህንነት አባላት ላይ የሞት ፍርድ አስተላለፈ።

የ36 ዓመቱ አስተማሪ አሕመድ አል ክሄር፤ በእስር ላይ ሳለ ይህችን ዓለም የተሰናበተው ባሳለፍነው ዓመት በፈረንጆቹ የካቲት ወር ነበር። አሕመድ የቀድሞ አገሪቷ ፕሬዚደንት ኦማር አል በሽር ተቃውሞ ላይ በመሳተፉ ነበር ለእስር የተዳረገው።

ባለፈው ሚያዚያ ወር በሽር ከሥልጣን ከተወገዱ በወራት ውስጥ እንዲህ ዓይነት ፍርድ ሲተላለፍ ይህ የመጀመሪያው ነው። አቃቤ ሕግ የሞት ፍርዱን ተገቢ ቅጣት ነው ብለውታል።

ፍርዱ ከተላለፈ በኋላም፤ ዳኛው የአሕመድን ወንድም፣ ስአድን 29ኙ የደህንነት አባላት ይቅርታ እንዲደረግላቸው ይፈልግ እንደሆነ ጠይቀውት ነበር። እርሱ ግን እንዲገደሉ እንደሚፈልግ ተናግሯል። የተከሳሾቹ ጠበቃ በበኩሉ ይግባኝ እንደሚል ገልጿል።

ፍርድ ቤቱ ባገኘው ማስረጃ፤ መምህር አሕመድ አል ክሄር፤ በአገሪቷ ምስራቃዊ ግዛት ካሳላ በእስር ላይ በነበረበት ወቅት በደህንነት አባላቱ ድብደባ ተፈፅሞበታል። ለስቃይም ተዳርጓል።

የመምህር አሕመድ ጉዳይ በመላ አገሪቷ ትኩረትን የሳበ ነበር። ግድያውም በ75 ዓመቱ ፕሬዚደንት አል በሽር ላይ ተቃውሞ አስነስቷል። ውሳኔውን ለመስማትም በዋና መዲናዋ ካርቱም አቅራቢያ በምትገኘው ኦምዱርማን ከተማ ፍርድ ቤት ውጭ በርካቶች ተሰባስበው አካባቢውን አጨናንቀውት ታይተዋል።

ሱዳን በቀድሞው ፕሬዚደንት ኦማር አል በሽር አገዛዝ ሥር፤ በአውሮፓዊያኑ 2018 በሁለት ግለሰቦች ላይ የሞት ፍርድ አስተላልፋ፤ ቅጣቱን ፈፅማለች።

በሱዳን ለወራት በቆየው ተቃውሞ ቢያንስ 170 ሰዎች ተገድለዋል። በመጨረሻም ኦማር አል በሽር ለ30 ዓመታት ከዘለቀው መንበራቸው በወታደራዊ ኃይሉ ከሥልጣናቸው ተወግደዋል።

በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ የቀድሞ ፕሬዚደንቱ ከሳዑዲ ልዑል መሐመድ ቢን ሰልማን ከተቀበሉት 25 ሚሊየን ዶላር ጋር በሚያያዝ የሙስና ወንጀል ሁለት ዓመታትን በእስር እንዲያሳልፉ ተፈርዶባቸዋል። ፍርድ ቤቱ በማረሚያ ቤት እንዲቆዩም ውሳኔ አስተላልፏል።

አል በሽር ግን ከሳዑዲው ልዑል የተቀበሉትን ገንዘብ አስመልክቶም ከሳዑዲ ጋር ባላቸው ስትራቴጂካዊ ግንኙነት የተበረከተ እንደሆነ ገልፀው፤ "ለግል ጥቅም ሳይሆን ለእርዳታ የተሰጠ ነው" ሲሉ በክሱ ላይ ቅሬታቸውን አሰምተዋል።

አል በሽር እርሳቸውን ወደ ሥልጣን ካወጣቸውና በአውሮፓዊያኑ 1989 ከተደረገው መፈንቅለ መንግሥት፣ ከዘር ማጥፋት እና የተቃዋሚዎች ግድያ ጋር በተያያዘም ሌሎች ክሶችም አሉባቸው።