ቦትስዋና፡ የምርምሩን ዝሆን የገደሉት አዳኞች ፈቃዳቸውን ተነጠቁ

በቦትስዋና ሁለት አዳኞች የምርምር ዝሆን መግደላቸውን ተከትሎ ፈቃዳቸው ተነጥቋል።

ሚሸል ሊ ፖተርና ኬቪን ሻርፕ የተባሉት አዳኞችም በሃገሪቱ መንግሥት ትዕዛዝ መሰረት የአደን ፈቃዳቸውን አስረክበዋል።

ለረዥም ጊዜያት የዝሆን አደንን ከልክላ የነበረችው ቦትስዋና ከጥቂት ወራት በፊት ነበር እንደገና የፈቀደችው።

ዝሆኖች በመንደሮች ውስጥ ባሉ እርሻዎች ውስጥ በመግባት እህሎችን በማበላሸት እንዲሁም ሰዎችን እየገደሉ ስላስቸገሩም ነው አደኑ እንደገና ፈቃድ ያገኘው።

ነገር ግን አሁን የተገደለው ይህ ዝሆን የምርምር በሚል ጥበቃ እንዲደረግለት ተወስኖ ነበር።

በቦትስዋና የሚገኙ ዝሆኖች ቁጥር ወደ 130ሺ ይጠጋል።

ዝሆኑ መገደሉን ተከትሎ ቅዳሜ እለትም የቦትስዋና መንግሥት ባወጣው መግለጫ "ሚሼል ሊ ፖተር እስከ መጨረሻው ድረስ የአደን ፈቃዱ የማይመለስለት ሲሆን የሌላኛው አዳኝ ኬቪን ሻርፕም ለሶስት አመት የሚወሰድበት ይሆናል" ተብሏል።

የሁለቱ አዳኞች ዜግነት ያልተገለፀ ሲሆን፤ ግለሰቦቹም ለቢቢሲ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ዝሆኑ አንገቱ ላይ አድርጎት የነበረውን ቀበቶ እንዲተኩ የተጠየቁ ሲሆን አንገቱ ላይ አጥልቆት የነበረው ቀበቶ እንዴት እንደተበላሸ የተገለፀ ነገር የለም።

ከዚህ ቀደም መንግሥት ባወጣው መግለጫ ዝሆኑ ፊት ለፊት ቆሞ ስለነበር አጥልቆት የነበረውን ቀበቶ ማየት እንዳልቻሉ አዳኞቹ መናገራቸውን አትቷል።

"ዝሆኑ ከወደቀ በኋላ ግን ቀበቶውን ማየት እንደቻሉና የምርምርም መሆኑን መረዳታቸውንም መናገራቸው" በመግለጫው ተካትቷል።

ነገር ግን ይህ አሳማኝ እንዳልሆነ የካላሃሪ የጥበቃ ማህበር ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል አሳውቋል፤ ለዚህም እንደምክንያትነት የሰጡትም የዝሆን ቀበቶ በጣም ትልቅና ከየትም አቅጣጫ እንደሚታይ በመግለፅ ነው።

ሮይተርስ በበኩሉ እንደዘገበው ሁለቱ አዳኞች ቀበቶውን ያበላሹት ማስረጃ ለመደበቅ ሲሞክሩ እንደሆነ ነው።

አብዛኛዎቹ ዝሆኖች በሃገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል የሚገኙ ሲሆን በናሚቢያ፣ ዛምቢያና ዚምባብዌን በሚያዋስነው ድንበር በነፃነት ይንቀሳቀሳሉ።

በአፍሪካ ውስጥ 415ሺ የሚገመቱ ዝሆኖች የሚገኙ ቢሆንም ባለው የህገወጥ አደን ምክንያት ቁጥራቸው እያሽቆለቆለ ነው ተብሏል።