የአየርላንድ ዜግነት ያላት የአይኤስ አባል የነበረችው ሴት ወደ ሃገሯ ልትመለስ ነው

የፎቶው ባለመብት, የአይኤስ አባል የነበረችው ሴት ወደ አየርላንድ ልትመለስ ነው
የአየርላንድ ዜግነት ያላት አይኤስ የተሰኘው ቡደን አባል የነበረች ሴት ወደ አየርላንድ ልትመለስ ነው ሲል የሃገሪቱ ቴሌቮዥን ጣቢያ ዘግቧል።
ሊሳ ስሚዝ የተሰኘችው አይሪሽ እና ሴት ልጇ አሁን ካሉበት ቱርክ አርብ ዕለት አየርላንድ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ሴትየዋ በፖሊስ ተይዛ ከሽብር ጥቃቶች ጋር በተያያዘ ቃለ-መጠይቅ ይደረግላታል ተብሎ ይጠበቃል።
የሊሳ ልጅ ሁለት ዓመቷ ሲሆን የተወለደችው ሶሪያ ቢሆንም ዜግነቷ ግን አየርላንዳዊ ነው ተብሏል።
ወ/ሮ ሊሳ የቀድሞ የአየርላንድ መከላከያ ሠራዊ ት አባል ናት።
ግለሰቧ በየትኛውም ዓይነት የአይኤስ ጥቃት ላይ እጇ እንደሌለና ሴት ልጆችን መሣሪያ አስታጥቃ እንዳላሰጠነች ትናገራለች።
አልፎም የአሜሪካው ወንጀል ምርመራ መሥሪያ ቤት ኤፍቢአይ ከአንድም ሁለት ሶስቴ አግኝቶ ምርመራ እንዳደረገባትና አሻራዋንና የዘረ-መል ቅንጣት እንደወሰደ ታስረዳለች።
ሊሳ እና የሁለት ዓመት ልጇ ሶሪያ ውስጥ በሚገኝ አንድ የስደተኞች መጠለያ ጣብያ ውስጥ ሲኖሩ ነበር።
የአየርላንዷ ጠቅላይ ሚኒስትር ፅ/ቤት ግለሰቧ ወደ አየርላንድ የምትመለስ ከሆነ ከፖሊስ ምርመራ እንደማትተርፍ ማሳወቁ አይዘነጋም።












