የኮንጎ አማጺያን መሪው ቦስኮ ንታጋንዳ የ30 ዓመት እስር ተፈረደበት

Ntaganda

የፎቶው ባለመብት, AFP

የቀድሞ የኮንጎ የአማጺያን መሪው ቦስኮ ንታጋንዳ ፈጽሞታል ለተባለው የጦር ወንጀል እና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች የ30 ዓመት እስራት ተበየነበት።

ለቦስኮ ንታጋንዳ ታማኝ ናቸው የተባሉ ታጣቂዎች በንጹሃን ዜጎች ላይ አሰቃቂ ድርጊቶችን መፈጸማቸውን የዓለም አቀፍ ወንጀለኞች ፍርድ ቤት ሐምሌ ወር ላይ አሳውቆ ነበር።

"ተርሚኔተር" በሚል ቅጽል ስሙ የሚታወቀው ንታጋንዳ በ18 የክስ መዝገቦች ጥፋተኛ የተባለ ሲሆን ከእነዚህም መካከል ግድያ፣ አስገድዶ የመድፈር፣ ሴቶችን የወሲብ ግዞተኛ ማድረግ እና ህጻናትን ለውትድርና መመልመል የሚሉ ይገኙበታል።

ዓለም አቀፉ የጦር ወንጀለኞች ፍርድ ቤት እስካሁን ካስተላለፋቸው ቅጣቶች ይህ ረዥሙ መሆኑም ተነግሯል።

ትውልደ ሩዋንዳዊው ቦስኮ ንታጋንዳ የ46 ዓመት ጎልማሳ ሲሆን በሩዋንዳ እና በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በተፈጸሙ በርካታ ግድያዎች እና ግጭቶች ተሳታፊ ነበር።

እአአ 2013 ላይ ሩዋንዳ በሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ እጅ መስጠቱ ይታወሳል።

Presentational white space

ቦስኮ ታጋንዳ ማነው?

  • እአአ 1973* የተወለደ ሲሆን ትውልድ እና እድገቱ ሩዋንዳ ነው
  • የእሱ ጎሳ አባላት በሆኑ የቱትሲዎች ላይ የዘር ጭፍጨፋ ሲካሄድ ጥቃቱን ሸሽት ወደ ዲሞክራቲክ ኮንጎ አምርቶ ነበር
  • እድሜው 17 ዓመት ሳለ የአማጺ ቡድንን በመቀላቀል በኮንጎ እና ሩዋንዳ የሽምቅ ውጊያ ላይ ተሳትፎውን ጀመረ
  • እአአ 2002-3 ድረስ በኮንጎ ኢቱሪ በምትሰኝ ግዛት የአማጺያን መሪ ነበር
  • 2008 ላይ 150 ሲገደሉ ትዕዛዝ የሰጠው ቦስኮ ንታጋንዳ ነበር
  • ንታጋንዳ ከአሁኑ የሩዋንዳ ፕሬዝደንት ፖል ካጋሜ አመራር ስር ሆኖ አብሮ ስርቷል
  • 2009 የኮንጎን ጦር በመቀላቀል የጀነራል ማዕረግን ማግኘት ችሎ ነበር
  • 2012 ላይ ጦሩን ከድቶ በመውጣት አዲስ አመጽ ቀስቅሶ ከ800 ሺህ በላይ ሰዎች እንዲፈናቀሉ ምክንያት ሆኖዋል።
  • 2013 ላይ በሩዋንዳ በሚገኘው አሜሪካን ኤምባሲ እጁን ሰጠ
  • 2019 ላይ በዓለም አቀፍ ወንጀለኞች ፍርድ ቤት ጥፋተኛ ተብሎ የ30 ዓመት እስር ተፈረደበት።
Presentational white space

አቃቢ ሕጎች ባቀረቡት ክስ ንታጋንዳ የኮንጎ አርበኞች ሕብረት የተረሰኘው ፓርቲ የጦር ሠራዊት ክንፍ ዘመቻዎች እና እቅዶችን ይመራ ነበር።

ይህ አማጺ ቡድን የሄማ ጎሳ አባል አይደሉም በተባሉ ግለሰቦች ላይ የጭካኔ እርምጃ ይወስድ ነበር ሲል የዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ያትታል።

በአንድ የሙዝ እርሻ ላይ በተፈጸመ ጥቃት 49 ሰዎች መገደላቸው የተረጋገጠ ሲሆን ሰዎቹ በዱላ፣ በቢላዋ እና በገጀራ ተደብድበው እና ተቆራርጠው እንዲገደሉ ተደርጓል ይላል የፍርድ ቤቱ መዝገብ።

"የወንዶች፣ ሴቶች እና ህጻናት አስከሬን በሙዝ እርሻው ላይ ተገኝቷል። አንዳንዶቹ አስክሬኖች እርቃናቸውን ነበሩ። የአንዳንዶቹ እጃቸው የፊጥኝ ታስሯል፤ የአንዳንዶቹ ጨንቅላት ፈርጧል" ሲሉ የፍርድ ቤቱ ዳኛ ፍሬመር ተናግረዋል።

የቦስኮ ንታጋንዳ አማጺ ቡድን በሚንቀሳቀስበት ቀጠና ከ1999 ጀምሮ ከ60 ሺህ በላይ ሰዎች ተገድለዋል።

የፍርድ ቤቱ ዳኞች ቦስኮ ንታጋንዳ አንድ የካቶሊክ ቄስ ገድሏል ሲሉም ማስረጃ አቅርበውበታል።