በኬንያ በ10 ዓመት ጊዜ ውስጥ የሕዝብ ቁጥር 9 ሚሊዮን ጨመረ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2019 የተደረገው የኬንያ የሕዝብ ቆጠራ ዛሬ ይፋ ተደርጓል።
የዘንድሮው ሕዝብ ቆጠራ ካለፈው ቆጠራ ጋር ሲነጻጸር በ10 ዓመት ጊዜ ውስጥ ኬንያ 9 ሚሊዮን ተጨማሪ ኬንያዊያንን አግኝታለች ተብሏል። አጠቃላይ የሕዝብ ብዛቷም ወደ 47.5 ሚሊዮን ማደጉ ታውቋል።
ይህ የሕዝብ ቆጠራ ከነጻነት በኋላ ኬንያ ያደረገችው ስድስተኛ የሕዝብ ቆጠራ ሲሆን ያለወረቀት የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በመጠቀም የተደረገ ነው።
ከእስካሁኑ ቆጠራ በተለየ መልኩም በዚህኛው ቆጠራ ወንድም ሴትም ያልሆኑ (intersex) ዜጎች ራሳቸውን ከሁለቱም ጾታ አግልለው ተቆጥረውበታል።
የአገሪቱ ብሔራዊ ስታትስቲክስ ቢሮ ይፋ ያደረገው መረጃ እንደሚያመለክተው በቆጠራው ውጤት 24 ሚሊዮን ሴቶች፣ 23.5 ሚሊዮን ወንዶችና ከ1500 በላይ ወንድም ሴትም ያልሆኑ ዜጎች የኬንያ የጾታ ስብጥር መሆኑ ታውቋል።
አገሪቱ ካሏት 47 ግዛቶች መካከል ብዙ ሕዝብ የሚኖርባት ግዛት በመሆን መዲናዋ ናይሮቢ ቀዳሚ ሆናለች። 4.4 ሚሊዮን ሕዝብም በመዲናዋ ይኖርባታል ተብሏል።
ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ የሕዝብ ቁጥሩ ይፋ መደረጉን ተከትሎ "የተጨመረው የሕዝብ ቁጥር የልማት ፖሊሲያችንንና ፕሮግራማችንን እንደገና ለመከለስ መሳሪያ ይሆነናል" ብለዋል።












