ቡልጋሪያ ከ እንግሊዝ፡ የዩሮ 2020 ማጣሪያ ውድድር በደጋፊዎች ዘረኛ ስድብ የተነሳ ሁለቴ መቋረጡ ተሰማ

እንግሊዝ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የእንግሊዝ ቡድን ኃላፊዎችና ተጫዋቾች ስታዲየሙን ለቅቀው መውጣት ፈልገው የነበረ ቢሆንም ቆይተው ጨዋታውን አጠናቅቀዋል

እንግሊዝ ለዩሮ 2020 ማጣሪያ በቡልጋሪያ፤ ሶፊያ ከተማ እያደረገች የነበረው ግጥሚያ ላይ የታደሙ የቡልጋሪያ ደጋፊዎች ዘረኛ የሆኑ ምልክቶችን በማሳየታቸውና ድምጾችን በማሰማታቸው የተነሳ ጨዋታው ሁለት ጊዜ መቋረጡ ተሰማ።

በስታዲየሙ የነበሩት ደጋፊዎች የናዚ ሰላምታ ምልክት ያሳዩ ሲሆን እንደ ዝንጀሮ ይጮሁ እንደነበርም ተነግሯል።

ጨዋታው መጀመሪያ የተቋረጠው እንግሊዝ 2 ለ 0 እየመራች ሳለ በ28ኛው ደቂቃ ላይ ነበር።

በዚህ መካከል ስታዲየሙ ውስጥ በድምፅ ማጉያ ደጋፊዎች ከእንደዚህ አይነት ተግባራቸው እንዲታቀቡ መልዕክት የተላለፈ ቢሆንም፤ ነውጠኛ ደጋፊዎቹ ግን በድርጊታቸው ገፍተውበታል።

በ43ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታው በድጋሚ ተቋርጧል።

በዚህ ጨዋታ እንግሊዝ 6 ለ 0 የረታች ሲሆን ምድብ ሀ ላይ በመሪነት ስፍራውን ይዛ ትገኛለች።

የእንግሊዝ የእግር ኳስ ማህበሩ ሊቀመንበር ግሬክ ክላርክ በስፍራው የነበሩ ሲሆን የተፈጠረውንም መታዘብ ችለዋል። የቡልጋሪያ ደጋፊዎች ተግባር በርካታ እንግሊዛዊያን ተጫዋቾችንና የቡድኑን አባላት ያስቆጣ ነው ብለዋል።

"በርካታ ዘረኛ የሆኑ ድምጾችን ሰምቻለሁ" ካሉ በኋላም "50 የሚሆኑ ሰዎች በቡድን በመሆን ጥቁር ለብሰው የፋሺስት ምልክት ሲያሳዩ ተመልክቻለሁ፤ እርግጠኛ መሆን ባልችልም ካለሁበት በ100 ሜትር ርቀት ላይ ነበር ምልክቱን የሚያሳዩ ደጋፊዎች የነበሩት" ብለዋል።

አክለውም የአውሮፓ እግር ኳስን የሚያስተዳድረው አካል በእለቱ ስለተፈጠረው ጉዳይ ጥልቅ ምርመራ ማድረግ እንዳለበትም ሃሳባቸውን ሰጥተዋል።

የቡልጋሪያ ደጋፊዎች የቀኝ ክንፍ ምልክቶችን ሲያሳዩ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በስታዲየም ወስጥ የተወሰኑ ደጋፊዎች የናዚ ምልክትን ሲያሳዩ ነበር

በጨዋታው ወቅት የተፈጠረምን ነበር?

የእንግሊዙ ተከላካይ በቁጥጥሩ ስር የነበረውን ኳስ ካሻገረ በኋላ ከደጋፊዎች የሰማው ድምፅ ምን እንደሆነ ለማጣራት ዞረ፤ ከዚያም በደቂቃዎች ውስጥ ጨዋታው ቆመ።

አጥቂው ሀሪ ኬን ከጨዋታው ዳኛ ኢቫን ቤቤክ ጋር ከተነጋገረ በኋላ በስታዲየሙ ውስጥ የተሰማውን ዘረኛ ንግግር የሚያወግዝ መልዕክት በድምፅ ማጎያ ተላለፈ። በዚሁ ሰዓት የቡድኑ ኃላፊ የተወሰኑ ተጫዋቾችን እያነጋገሩ ነበር።

ከዚያም ጨዋታው እንዲቀጥል ቢደረግም የእረፍት ሰዓት ከመድረሱ አስቀድሞ በድጋሚ ሊቋረጥ ችሏል።

ጨዋታው እንደገና ከመጀመሩ በፊት የቡድኑ ኃላፊ ከተጫዋቾቹ ጋር ተነጋግረዋል።

የተወሰኑ ፊታቸውን የሸፈኑና ጥቁር የለበሱ የቡልጋሪያ ቡድን ደጋፊዎች፤ ጨዋታው ከእረፍት ከመመለሱ በፊት ስታዲየሙን ጥለው ወጥተዋል።

ቢቢሲ ሬዲዮ 5 እንደዘገበው የተወሰኑት ዘረኛ እና የቀኝ ክንፍ አክራሪ ምልክቶችን ሲያሳዩ ነበር።

እንግሊዝ በ2020 የአውሮፓ ማጣሪያ ጨዋታ ወቅት ዘረኛ መልዕክቶችን ስታስተናግድ ይህ የመጀመሪያዋ አይደለም። ከሞንቴኔግሮ ጋር በነበራትና 5 ለ 1 ባሸነፈችበት ጨዋታም እንዲሁ ዘረኛ የሆኑ መልዕክቶች በእንግሊዝ ተጫዋቾች ላይ ተሰንዝሯል።

በዚህም የተነሳ ሞንቴኔግሮ 20ሺህ ዩሮና ሁለት ጨዋታዎችን ደጋፊዎቿ በሌሎበት ዝግ ስታዲየም እንድታካሄድ ተቀጥታለች።