የላይቤሪያ ፖሊስ ፕሬዝዳንት ዊሃን የሚተቸውን የሬዲዮ ጣቢያ ዘጋ

ፕሬዝዳንት ጆርጅ ዊሃ

የፎቶው ባለመብት, EPA

ላይቤሪያ ውስጥ አድማ በታኝ ፖሊሶች በበርካቶች ተወዳጅ የሆነውንና የቀድሞውን ኮከብ እግር ኳስ ተጫዋች እና የአሁኑን ፕሬዝዳንት ጆርጅ ዊሃን በመተቸት የታወቀውን ሬዲዮ ጣቢያ ዘጉ።

ፖሊሶቹ ሩትስ ኤፍ ኤም የሚባለውንንና በዋና ከተማዋ ሞንሮቪያ የሚሰራጨውን ሬዲዮ ጣቢያ ሰብረው በመግባት ነው ስርጭቱን ያቋረጡት።

ጣቢያው በተዘጋበት ወቅት ህዝቡ እየተሰቃየ ፕሬዝዳንቱ ለብክነት የተጋለጠ ወጪ እያወጡ እንደሆነ የሚያወሳ የጠዋት ፕሮግራም እየተሰራጨ ነበር ተብሏል።

የሃገሪቱ የፍትህ ሚኒስትር ፍራንክ ሙሳ ዲን ለቢቢሲ እንዳረጋገጡት ከላይቤሪያ ቴሌኮሚዩኒኬሽን ባለስልጣን የተጠቀሰው የሬዲዮና ሌሎች ሁለት ጣቢያዎች ፍቃድ ሳያገኙ በመስራት ላይ መሆናቸውን የሚገልጽ ደብዳቤ እንደደረሳቸው ፖሊሶች መላካቸውን ገልጸዋል።

በሕግ እንደሚጠበቀው መንግሥት ጉዳዩን ለምን ወደ ፍርድ ቤት በመውሰድ መፍትሄ እንዲገኝ እንዳላደረገ ሚኒስትሩ ምላሽ አልሰጡም።

ፖሊሶች የጣቢያውን በር ሰብረው ለመግባት በሚሞክሩበት ጊዜ ከአሜሪካ በመሆን በኢንተርኔት ወይይቱን እየመራ የነበረው የጣቢያው ባላቤት ሄንሪ ኮስታ አድማጮቹ ጣቢያውን መጥተው እንዲያድኑ ጥሪ አድርጎ ነበር።

የዓይን ምስክሮች እንደተናገሩት ባለቤቱ ላቀረበው የድረሱልኝ ጥሪም በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ከ400 የሚበልጡ ሰዎች ደርሰው ነበር፤ ነገር ግን ይህ ፖሊስ ጣቢያው ስርጭቱን እንዲያቆም ከማድረግ አላገዳቸውም።

በአካባቢው የነበሩ ሰዎች ለቢቢሲ እንደተናገሩት የጣቢያው ስርጭት ከተቋረጠ በኋላ ፖሊሶች የማሰራጫ መሳሪያዎችን በመኪና ላይ ሲጭኑ መመልከታቸውን መስክረዋል።

የቀድሞው እግር ኳስ ተጫዋች ጆርጅ ዊሃ የላይቤሪያን የፕሬዝዳንትንት መንበር በያዙበት ባለፉት ከሁለት ዓመታት ሩትስ ኤፍ ኤም ከፕሬዝዳንቱ ጋር ያለው ግንኙነት ጥሩ የሚባል አልነበረም።

ሬዲዮ ጣቢያው ዛሬ ከመዘጋቱ በፊት የሃገሪቱን የሬዲዮ ስርጭት ሕግን አክብሮ እየሰራ መሆኑንና ፈቃዱ እንዲታደስለት ጥያቄ ማቅቡንም ተናግሮ ነበር።