ድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳን ምን አጋጠመው?

ድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ

ታዋቂው የኦሮምኛ ድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ አዲስ አበባ ውስጥ በአንድ ጎዳና ላይ በመኪና እየተከተሉ ሲሰድቡኝ ነበር ካላቸው ሰዎች ጋር አለመግባባት ውስጥ ገብቶ እንደነበር ተናገረ።

ሃጫሉ ማንነታቸው ካልታወቁ ሰዎች ጋር ሲነጋገርና ሌሎች ሰዎች ደግሞ ለመገላገል ሲጥሩ የሚያሳይ ቪዲዮ በማሕበራዊ መገናኛ መድረኮች ላይ በስፋት ሲዘዋወር ቆይቷል።

ነገሩ የተከሰተው ሜክሲኮ አካባቢ በተለምዶው ኮሜርስ የተባለው ስፍራ ላይ እንደሆነ በተንቀሳቃሽ ምስሉ ላይ ይታያል።

አንዳንዶች ድምጻዊው ጥቃት እንደተፈጸመበት ቢናገሩም በቪዲዮው ላይ እንደሚታየውና እርሱም እንደሚናገረው "ስሜታዊ ከሚያደርጉ" የቃላት ልውውጥ በስተቀር ጉዳት የሚያስከትል ጸብ አልነበረም።

ክስተቱን በሚያሳየው ተንቀሳቃሽ ምስል ላይ ድምጻዊው ከመኪናው ወርዶ በሚናገርበት ጊዜ ሌሎች ሰዎች ለመገላገል ሲሞክሩና ሌሎች ሰዎችም በስፍራው ሲሰበሰቡ ይታያል። በተጨማሪም መኪናው የቆመው ሌሎች ተሽከርካሪዎች በሚያልፉበት ቦታ ላይ በመሆኑ መንገድ የተዘጋባቸው መኪኖች የጡሩምባ ድምጽ ይሰማል።

በአካባቢው የነበሩ ሰዎች ሃጫሉን ወደመኪናው እንዲሄድ ሲያግባቡት በንዴት "ዐብይ ላይ ነው . . . " በማለት በቁጣ ስሜት ሲናገር ይደመጣል።

ድምጻዊው እንደሚለው ድርጊቱ ያጋጠመው ማክሰኞ ዕለት ሲሆን ከአፍሪካ ኅብረት ጽህፈት ቤት ጀምረው ግለሰቦቹ እየተከታተሉ እስከሜክሲኮ ድረስ ሲሰድቡት እንደነበረ ገልጿል።

ለቢቢሲ ሲናገር "እኔ ሰውን አከብራለሁ ነገር ግን እንዲህ መብቴን የሚጥስ ነገር ሲገጥመኝ ከማንም ፈቃድ አልጠይቅም" በማለት የሰዎቹ ድርጊት እንዳስቆጣው ጠቅሷል።

ግለሰቦቹ ይሰንዝሯቸው የነበሩት ቃላት ስሜት ውስጥ የሚያስገቡ ስለነበሩ ሜክሲኮ አካባቢ መኪናውን አቁሞ ሲከተሉኝ ነበር ያላቸው አራት ሰዎች ወደነበሩበት ሊያናግራቸው መሄዱንና ሰዎች መሰብሰባቸውን ይናገራል።

"የሰዎቹን ንግግር በዝምታ ማለፍ አስቸጋሪ ነበር" የሚለው ሃጫሉ "ፍላጎታቸው በሚሰነዝሯቸው ቃላት ስሜታዊ በማድረግ አምባ ጓሮ ለመፍጠር ነበር" ይላል።

ድምጻዊው ሃጫሉ እንደሚለው እንዲህ አይነቱ አጋጣሚ እንደተደጋገመበትና በዚህ ወር ውስጥ ይህ ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑንም ተናግሯል።

እንዲህ አይነቱን ድርጊት የሚፈጽሙ ሰዎች ላይ መንግሥት ተገቢውን እርምጃ በመውሰድ ሥርዓት አልበኝነትን ለማስቆም የሚጠበቅበትን ማድረግ አለበት ብሏል።

ጎዳና ላይ ከተከሰተው ከዚህ ውዝግብ በኋላ ፖሊስ ከስፍራው በመድረስ እንደገላገላቸውና ለገሐር አካባቢ ወደሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ ሄደው ግለሰቦቹ ጥፋተኛ መሆናቸውን አምነው ተለቅቀዋል ሲል ይናገራል።

ግለሰቦቹ ይሰነዝሩት የነበሩት ቃላት ከጥላቻ የመነጩና ስሜታዊ ያደርጉ እንደነበር ሃጫሉ ቢናገርም ከግለሰቦቹ ጋር ወደ ፖሊስ ጣቢያ ከሄዱ በኋላ ነገሩ በቀላሉ ማብቃቱን ገልጿል።

በክስተቱ ወቅት እርሱም መንገድ በመዝጋቱ ይቅርታ መጠየቁንና ተገቢ ያልሆኑ ቃላት ሰንዝረዋል የተባሉት ግለሰቦችም ይቅርታ እንደጠየቁ ሃጨዓሉ ለቢቢሲ አስረድቷል።