የፍሎሪዳ ዳኛ፡ እንቅልፍ ጥሎት ከችሎት የቀረው 'ዳኛ' ለእስር ተዳረገ

የፎቶው ባለመብት, Inpho
እንቅልፍ ጥሎዎት በሕይወትዎ ያመለጥዎት መልካም እድል አሊያም የተቀጡበት አጋጣሚ ይኖር ይሆናል። ከወደ ፍሎሪዳ የተሰማው ግን በርካቶችን ያነጋገረ ነው።
እንቅልፍ ጥሎት ከተራው ህዝብ ተመርጠው ለዳኝነት ከሚቀመጡ ግለሰቦች(ጁሪ) መካከል ከችሎት የቀረው አንደኛው 10 ቀናትን በእስር እንዲያሳልፍ ተበይኖበታል።
ከዌስት ፓልም ቢች የመጣው የ21 ዓመቱ 'ዳኛ' ዲንድሬ ሶመርቪሌ ዳኛ ሆኖ እንዲያገለግል የተመረጠው ባሳለፍነው ነሃሴ ወር ነበር።
ዲንድሬ ከተራው ህዝብ ተመርጠው ለዳኝነት ከሚቀመጡ ግለሰቦች (ጁሪ) ስድስት 'ዳኞች' አንዱ ሲሆን ችሎቱ የመጀመሪያው ነበር።
ይሁን እንጂ ገና በመጀመሪያው ቀን የፍርድ ቤት ውሎ እንቅልፍ ጥሎት በትንሹ ለሁለት ሰዓታት ያህል የፍርዱን ሂደት አስተጓጉሎታል። ይህም ሲሆን ፍርድቤቱን አላሳወቀም ተብሏል።
ግለሰቡን ፍርድ ቤት ያቆሙት ዳኛ ጆን ካሰትሬኔክስ ከ10 ቀናት እስሩ በተጨማሪ 150 ሰዓታት ከማህበራዊ አገልግሎት እንዲታገድ እና 223 ዶላር የገንዘብ ቅጣት እንዲጣልበት ወስነዋል።
የተጣለበትን ጊዜ በእስር ያሳለፈው ግለሰብ ውሳኔው የተጋነነ ነው ሲል በፍርዱ ላይ ቅሬታውን አሰምቷል።
ባሳለፍነው አርብ ፍርድ ቤት ከቀረበ በኋላ "አሁን ስሜ በጥፋት ተመዝግቧል፤ ወንጀለኛ እንደሆንኩ ነው የሚሰማኝ። ከዚህ በኋላ ለሚዲያ በምሰጠው እያንዳንዱ ቃለ ምልልስ ሁሉንም ነገር ማብራራት ይጠበቅብኛል" ሲል ለአገሪቷ መገናኛ ብዙሃን ተናግሯል።

የፎቶው ባለመብት, Palm Beach County Police
ዲንድሬ ለመገናኛ ብዙኃን እንዳስረዳው የማንቂያ ደወል ሞልቶ የተኛ ቢሆንም ከሰዓታት በኋላ ሲነቃ ችሎቱ የሚካሄድበትን ሰዓት እንደዘነጋው መገንዘቡን ያስረዳል።
በሰዓቱ ደንግጦ ስለነበር ስለ ሁኔታው ስልክ በመደወል ለፍርድ ቤቱ ሳያሳውቅ ቀርቷል።
እሱ አንደሚለው ከዚያ በኋላ በከተማዋ መናፈሻ እና መዝናኛ ክፍል ሥራ ስለነበረው ወደዚያው አምርቷል። ለድርጊቱ ቀላል ቅጣት ቢጠብቅም የከፋ ሆኖ አግኝቶታል።
ፖሊስ ግለሰቡ ከአያቶቹ ጋር የሚኖርበት ቤት ድረስ በመሄድ የመጥሪያ ወረቀቱን አቀብሎታል።
ወደ ፍርድ ቤቱም ካቀና በኋላ "እውነቱን ለመናገር አዎ እንቅልፍ ጥሎኝ ነበር፤ ግን ይህንን ያህል መዘዝ ያስከትላል ብየ አላሰብኩም" ብሏል።
አክሎም ከዚህ ቀደም በምንም ዓይነት ጉዳይ ፍርድ ቤት ቀርቦም ሆነ ታስሮ እንደማያውቅ አስረድቷል። ይሁን እንጅ ዳኛው ካስተርኔክስ ሃሳባቸውን አልወጡም። "አንተ ትመጣለህ በማለት በትንሹ ለአንድ ሰዓት ያህል ጠብቀንሃል፤ ግን አልመጣህም" ሲሉ ከውሳኔያቸው ፈቀቅ እንደማይሉ በአፅንኦት ገልፀዋል።
ዳኛው አክለውም 100 ቃላት የሚሆን የይቅርታ ደብዳቤ እንዲፅፍ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል።














