አራት የኤርትራ የእግር ኳስ ብሔራዊ ቡድን አባላት ኡጋንዳ ውስጥ ጠፉ

የኤርትራ ብሄራዊ ቡድን

የፎቶው ባለመብት, Uganda Football Federation

አራት የኤርትራ የእግር ኳስ ብሔራዊ ቡድን አባላት ኡጋንዳ ውስጥ መጥፋታቸው ታወቀ።

ከ20 ዓመት በታች የሴካፋ እግር ኳስ ውድድር ላይ ለመሳተፍ ወደ ኡጋንዳ ካቀኑት ተጫዋቾች መካከል አራቱ ወደ ሆቴላቸው ያልተመለሱ ሲሆን፤ ቅድመ ዝግጅት ለማድረግ በተዘጋጀው ልምምድ ላይም አልተገኙም ተብሏል።

የቢቢሲ ትግርኛ ክፍል ከምንጮቹ ማረጋገጥ እንደቻለው ከሆነ አራቱም ተጫዋቾች በኡጋንዳ የጥገኝነት ጥያቄ አቅርበዋል።

የውድድሩ አዘጋጅ ኮሚቴ ዋና ጸሃፊ የሆኑት ኤማብል ሃቢማና የተጫዋቾቹን መጥፋት ማረጋገጣቸውን የኡጋንዳ ሚዲያዎች የዘገቡ ሲሆን፤ እስካሁን የት እንደሚገኙ የታወቀ ነገር የለም ተብሏል።

ዋና ጸሃፊው ''አራቱም ተጫዋቾች ከማረፊያቸው ጠፍተዋል። ከክስተቱ በኋላ በሆቴሉ አካባቢ ያለውን ጥበቃ አጠናክረናል። ውድድሩ በጥሩ መንፈስ ተጀምሮ እንዲጠናቀቅ ነው የምንፈልገው'' ማለታቸውን ደይሊ ሞኒተር የተባለው የኡጋንዳ ጋዜጣ ዘግቧል።

የኤርትራ ብሔራዊ ቡድን እስካሁን ጥሩ እየተጫወተ የነበረ ሲሆን፤ ዛሬ ከሰአት ላይ በግማሽ ፍጻሜ ከኬንያ አቻው ጋር ተጫውቶ 1 ለምንም ተሸንፏል።

በሴካፋ ውድድር ስድስት ግቦችን በማስቆጠር ኮከብ ጎል አግቢነቱን እየመራ የሚገኘው ኤርትራዊው ማወል ተስፋይ በጉዳት ምክንያት በጨዋታው ላይ እንደማይሰለፍ ታውቋል። ምናልባትም ጥገኝነት ከጠየቁት አራት ተጫዋቾች መካከል ሊሆን እንደሚችልም ተገምቷል።

የተጫዋቾቹ መጥፋት ብሔራዊ ቡድኑ ላይ ምን አይነት ተጽዕኖ ሊኖረው እንደሚችል እስካሁን ባይታወቅም በውድድሩ እንደሚቀጥሉ ይጠበቃል።

ተጫዋቾቹ ሊጠፉ የቻሉት "ጉዳት አጋጥሞናል" ብለው በሆቴላቸው ከቀሩ በኋላ መሆኑንም ደይሊ ሞኒተር ዘግቧል።

የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ በቀሪ 14 ተጫዋቾች ውድድሩን የሚጨርሱ ሲሆን፤ የቀሩት ተጫዋቾች ግን በህምም ምክንያት ሊገኙ አልቻሉም ሲሉ ተደምጠዋል።

በተመሳሳይ እ.አ.አ. በ2015 አሥር የዋና ብሔራዊ ቡድኑ አባላት ወደ ቦትስዋና ከሄዱ በኋላ አንመለስም ማለታቸው ይታወሳል። በ2013ትም ዘጠኝ የሚሆኑ የቡድኑ አባላትና አሰልጣኙም ጭምር ኬንያ ውስጥ ተሰውረው ነበር።