ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሦስት ሚሊየን ሶሪያውያን ወደ አገራቸው ሊመለሱ ነው
ሶስት ሚሊየን የሶሪያ ስደተኞች ደህንነቱ የተጠበቀ ነው ወደ ተባለ ሰሜናዊ የሃገሪቱ ክፍል ሊመለሱ እንደሚችሉ የቱርኩ ፕሬዝዳንት አስታወቁ።
ራሲፕ ታይፕ ኤርዶጋን እንዳሉት ከማንኛውም አይነት አደጋ ነጻ የሆነው ክልል ከአሜሪካ ጋር በመተባባር የተዘጋጀ ሲሆን ደህንነቱ እስከሚረጋገጥ ድረስ ብዙ መጠበቅ አስፈልጓል።
በአሜሪካ የሚደገፉት የኩርድ ተዋጊዎች ቀደም ብሎ በቱርክ ድንበር በኩል ካለው የሶሪያ ሰርጥ ለቅቀው መሄዳቸው የሚታወስ ነው።
ቱርክ ደግሞ የኩርድ ተዋጊዎችን በአሸባሪነት ፈርጃቸዋለች።
የፕሬዝዳንት ኤርዶጋን ዕቅድ ይፋ የሆነው አንካራ ከሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን እና ከኢራኑ ፕሬዝዳንት ሃሳን ሮሃኒ ጋር ውይይት ካደረገች በኋላ መሆኑ ታውቋል።
ምንም እንኳን የኩርድ ተዋጊዎች ስለፕሬዝዳንቱ አስተያየት ያሉት ነገር ባይኖርም አምርረው እንደሚቃወሙት ግልጽ ነው ብሏል የቢቢሲው የሶሪያ ዘጋቢ አላን ጆንስተን።።
በያዝነው ወር መጀመሪያ ላይ ቱርክ ስደተኞቹን ወደ ሃገራቸው ለመመለስ በምታደርገው ጥረት ዓለማ አቀፍ ድጋፍ የማታገኝ ከሆነ ስደተኞቹ ወደ አውሮፓ አልፈው እንዲሄዱ ድንበሯን ክፍት እንደምታደርግ ገልጻ ነበር።
በ2016 ከአውሮፓ ህብረት ጋር በተደረሰ ስምምነት መሰረት ቱርክ በድንበሯ በኩል ስደተኞች ወደ አውሮፓ ለመግባት እንዳይሞክሩ ጠበቅ ያለ ጥበቃ ማድረግ እንዳለባት ተቀምጧል።
ቱርክ ይህንን በማድረጓና ከሶሪያ የሚመጡ ስደተኞችን በማስተናገዷ ከአውሮፓ ህብረት 6.6 ቢሊየን ዶላር እንደምታገኝ ቃል ተገብቶላት ነበር። ነገር ግን ፕሬዝዳንት ኤርዶአን ቃል ከተገባው ገንዘብ ግማሽ የሚሆነው ብቻ ነው የደረሰን ሲሉ ቅሬታቸውን አሰምተዋል።
የአውሮፓ ህብረት በበኩሉ 6.2 ቢሊየን ዶላር የሚሆነውን ገንዘብ ለቱርክ አስረክቢያለሁ ብሏል።
ቱርክ በ2011 የተጀመረውን የእርስ በእርስ ጦርነት ሸሽተው የወጡ ከ3.6 ሚሊየን በላይ ስደተኞችን በተለያዩ ማቆያዎች ይዛለች።
በቱርክ ድንበር በኩል የምትገኘው ኢድሊብ ግዛት በአማጺያን እና ኢስላማዊ ጂሃዲስቶች ቁጥጥር ስር በመሆኗ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ንጹሃን ዜጎች ማቄን ጨርቄን ሳይሉ ወደ ሰሜናዊ ሶሪያ ተሰድደዋል።