በፕሮቴስታንት እምነት ተከታይነቱ ለእስር ተዳርጎ የነበረው ኤርትራዊ ህይወቱ አለፈ

በአስመራ የሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ

የፕሮቴስታንት እምነት ተከታይ በመሆኑ ለእስር ተዳርጎ የነበረው ኤርትራዊው ተኪኤ ተስፋ ዮሃንስ በእስር ቤት ህይወቱ ማለፉን የእስረኞች የእምነት መብት ተሟጋች ድርጅት 'ሪሊዝ ኤርትራ' ዳይሬክተር ዶ/ር ብርሃነ አስመላሽ ለቢቢሲ ገልፀዋል።

በኤርትራዋ መዲና አስመራ በአንድ የግል መኖሪያ ቤት መቶ አርባ አንድ የሚጠጉ የእምነቱ ተከታዮች መንፈሳዊ ስብስባ ሊያካሂዱ ሲሉ የተያዙት ከአራት ወራት ገደማ በፊት ነበር። ተኪኤ በወቅቱ በቁጥጥር ስር ከዋሉት ውስጥ አንዱ እንደነበር ዶ/ር ብርሃነ ያስረዳል።

ግለሰቦቹ በሙሉ ዓዲ ዓቤቶ ወደተሰኘው እስር ቤት ተወስደው የነበረ ሲሆን፤ የተወሰኑት ሊፈቱ ችለዋል።

የአምሳ አምስት እድሜ ያለው ተኪኤ ባለትዳርና የሶስት ልጆች አባት ሲሆን ጠንካራ ሰራተኛም እንደነበር ጓደኛው ሃኒባል ዳንኤል ይናገራል። በአካል ጉዳኝነቱ ሳይበገር ሁለት አይነት ስራ እየሰራ ልጆቹንም እያሳደገ እንደነበር ምስክርነቱን ሰጥቷል።

"በእርግጥ ከተለያየን ረዥም ጊዜ ሆኖናል። ሆኖም በማውቀው ደረጃ ጠንካራ ሰራተኛና ምሬትም የማያውቅ ሰው ነበር" ብሏል።

ከኤርትራ ባለስልጣናት መረጃ ማግኘት ከባድ እንደሆነ የሚገልፀው አቶ ሃኒባል መሞቱ እንጂ ህይወቱ ከማለፉ በፊት ህክምና እርዳታ ይደረግለት አይደረግለት፤ እንዲሁም መቼ እንደሞተ የሚታወቅ ነገር የለም በማለት አስረድቷል።

በተመሳሳይም ከጥቂት ወራት በፊትም ፍፁም የተባለ ሌላ ወንጌላውያን እምነት ተከታይ በዳህላክ እስር ቤት ህይወቱን እንዳጣ ይናገራል።