ባንግላዴሽ የጋብቻ መመዝገቢያ ቅፅ ላይ "ድንግል" የሚለውን ቃል እንዲወጣ ወሰነች

በባንግላዴሽ የሚገኙ ሴቶች በጋብቻ ምዝገባ ወቅት "ድንግል" መሆናቸውንና አለመሆናቸውን በጋብቻ ቅፅ ላይ ማስፈር ይጠበቅባቸው የነበረ ሲሆን ከሰሞኑ ግን ፍርድ ቤቱ ይህ ተቀባይነት እንደሌለው ወስኗል።

የከፍተኛው ፍርድ ቤት በውሳኔው እንዳሳወቀው "ድንግል" የሚለው ቃል "ያላገባች" በሚል ይተካል ብሏል።

በቅፁ ላይ የሰፈረው ስለተጋቢዎች ከዚህ ቀደም መረጃ የሚጠይቀው የሞቱባቸውና የተፋቱ የሚለው ግን አይቀየርም።

የሴት መብት ተሟጋቾች "ድንግል" የሚለው ቃል የሚያዋርድ ነበር በማለትም በውሳኔው ጮቤ ረግጠዋል።

ፍርድ ቤቱ በተጨማሪ ወንዶች ተጋቢዎችም የጋብቻ ሁኔታቸውን ሊያሳውቁ እንደሚገባ ውሳኔ አስተላልፏል።

የእስልምና እምነት ተከታዮች ከፍተኛ ቁጥር ያላት ባንግላዴሽ የጋብቻ ህጓ በሴት መብት ተሟጋቾች ዘንድ ገዳቢና አግላይ እየተባለም ይተቻል።

ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ልጃገረዶችም በቤተሰቦቻቸው ምክንያት ያለእድሜያቸው ይዳራሉ።

ፍርድ ቤቱ ምን ወሰነ?

ፍርድ ቤቱ "ኩማኒ" የሚለው የቤንጋሊ ቃል ከጋብቻ መመዝገቢያ ቅፅ መውጣት አለበት ሲል ወስኗል። ቃሉ ያላገባችን ሴት የሚገልፅ ከመሆኑ በተጨማሪ "ድንግል" የሚል ትርጓሜ አለው።

በጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር 2014 የህግ ባለሙያዎች ቡድን የጋብቻ መመዝገቢያ ቅፁ አሳፋሪና የሴቶችን መብት የጣሰ ነው በማለት መከራከሪያ አቅርቦ ነበር።

እሁድ እለትም ፍርድ ቤቱ ቃሉን "ኦቢባሂታ" በሚል አሻሚ ትርጉም በሌለው ቃል እንዲተካ ወስኗል።

ውሳኔውም ከጥቂት ወራት በኋላ ተግባራዊ ይሆናል።

በጉዳዩ ላይ ተሳታፊ የነበረችው የህግ ባለሙያ አይኑን ናሃር ሲዱቅዋ ውሳኔውን አድንቃ ይህ ውሳኔም በባንግላዴሽ ያለውን የሴቶች መብት እንደሚያሻሽል ተስፋ አድርጋለች።

በአካባቢው ያለ የጋብቻ መመዝገቢያ ፅህፈት ቤት ሰራተኛ መሀመድ አሊ አክባር አዲሱ ቅፅ መቼ ተግባራዊ እንደሚሆን እንዲያሳውቋቸው ባለስልጣናቱን እየጠበቁ መሆናቸውን ገልፆ ከዚህ ቀደም ግን ወንዶች ስለ ጋብቻ ሁኔታቸው ምንም አይነት ጥያቄ ሳይመልሱ ሴቶች የሚገደዱበት አሰራር ለምን ተዘረጋ በሚል ብዙዎች ይጠይቁት እንደነበር ተናግሯል።

"እንዲህ አይነት ጥያቄዎች በምጠየቅበት ወቅት ከኔ ኃላፊነት በላይ ነው እል ነበር፤ ከዚህ በኋላ ግን ያንን አልመልስም" ብሏል።