"ህዝብ ከህዝብ ሊጋጭ አይችልም"የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ

የሶማሌ እና የኦሮሚያ ክልል ሕዝቦችን ወዳጅነት ለማጠናከር ያሰበ የወዳጅነት መድረክ ጅግጅጋ ላይ እየተካሄደ ነው። ዛሬ ጥዋት ሐምሌ 28፣ 2011 ዓ.ም በተጀመረው መድረክ ላይ የሁለቱም ክልል መሪዎች ተገኝተዋል።
በመድረኩ ላይም የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት ሙስጠፌ ሙሃመድ የሁለቱን ህዝቦች ግንኙነት በቋንቋ፣ ባህል እና ሃይማኖት ምን ያህል የተሳሰረ እንደሆነ ገልፀው ይህንን ለዘመናት የዘለቀ የሁለቱን ህዝቦች ግንኙነትም ለማጠናከር ከባለፈው አመት ወዲህ ተጠናክሮ እየተሰራ ነው ብለዋል።
ለዘመናት የሁለቱ ህዝቦች ግጭት ከግጦሽ መሬት ይገባኛል ጋር በተያያዘ ቢሆንም ባለፉት ጥቂት አመታት ግን ወዳልተለመደ አቅጣጫ አምርቷል ብለዋል።
የሁለቱ ክልሎችን የሚያዋስነው ድንበር ከ1400 ኪ.ሜትር በላይ መሆኑን አስታውሰው የግጦሽና የመሬት ይገባኛል ጥያቄ መፈታት ያለበት በሐገር ሽማግሌዎች እንጂ ሌላ መልክ መያዝ አልነበረበትም ብለዋል።
"በጠላት ተመርተን ወዳልተፈለገ ግጭት አናመራም" ብለዋል።
በሌላ በኩል የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ በበኩላቸው የሁለቱ ህዝቦች አብሮነት ለዘመናት የቆየ መሆኑን አፅንኦት በመስጠት ተናግረዋል።
"ኦሮሞ ሲከፋው መሸሸጊያ ያደርገው የነበረው ሶማሌውን ነው። ይህ ወንድማማችነት ወደተሻለ ደረጃ ማስተላለፍ ያለበት ደግሞ ይህ ትውልድ ነው" ብለዋል።
ምክትል ፕሬዚዳንቱ በንግግራቸውም የህዝብን ቀጣይነት አፅንኦት በመስጠት ተናግረዋል። "ህዝብ ከህዝብ ሊጋጭ አይችልም፤ ግለሰቦች ሊጋጩ ይችላሉ። በጎረቤት መካከል ግጭት ሊፈጠር ይችላል እንጂ ኦሮሞ ከሶማሌ ጋር ሊጋጭ አይችልም" ብለዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ባለፈው ዓመት በጅግጅጋ በተከሰተው ሁከት ጉዳት ከደረሰባቸው ቤተ-እምነቶች መካከል የሆነችው የኪዳነ ምህረት ቤተክርስቲያን እደሳዋ ተጠናቆ ዛሬ ትመረቃለች ተብሎም ይጠበቃል።
ቤተ ክርሰቲያኗ በሶማሌ ክልል መንግሥት እና በሌሎች አካላት ድጋፍ ነው የታደሰችው።












