'በእርግማን' የተፈጠረው የኮንሶው 'ኒው ዮርክ'

የፎቶው ባለመብት, BBC
በድሮ ዘመን ነው አሉ። ከዘጠኙ የኮንሶ ጎሣዎች አንዱ የሆነው የፋሻ ጎሣ ንጉሥ የነበሩት አልሞጌ ቤተሰብ አባል የሆነ አንድ ልዑል የንጉሣዊያን ቤተሰብ የማያደርገውን አደረገ፤ ሕግ ጣሰ።
ከሕብረተሰቡ መመሪያ አፈንግጦ ስህተት የሠራው ይህ ልዑል፤ 'የጎሣ መሪ የሆነ ንጉሥ ሁለት ሚስት ማግባት አይችልም' የሚለውን የኮንሶዎች ሕግ ተላልፎ ሁለት ትዳር መሠረተ።
የልዑሉ ድርጊት የሌሎች ጎሣ መሪዎችን ልብ አሳዘነ፤ አስቆጣቸውም። በዚህ ብቻ አላበቁም፤ 'ቅጣትም ይከትልሃል' ሲሉ በየኑ።
ብይኑ ደግሞ እንዲህ ይላል፤ 'ከዚህ በኋላ ንጉሥ መሆን አትችልም፤ ከክብርህ ወርደሃል፤ ልጅህ ሲያድግ ያንተን ቦታ ይተካ ይሆናል እንጂ የአንተ ንጉሥ የመሆን ጉዳይ አብቅቶለታል።'
በዚህ የተበሳጨው ልዑል በሕብረተሰቡ ታላቅ ክብር ያላቸው ሁለት ዕቃዎችን ከቤተሰቡ ሰርቆ ይሰወራል። የእጅ አንባር እና ከአውራሪስ ቀንድ የተሠራ ጥሩንባ።
ቀዬውን ለቆ ጉዞውን አሁን በተለምዶ 'ኒው ዮርክ' እየተባለው ወደሚጠራው ሥፍራ ያደርጋል። 'ኒው ዮርክ' የዚያን ጊዜ ለጥ ያለ ሜዳ ነበር አሉ። ሜዳማው ሥፍራ ላይ ሲደርስ የእጅ አንባሩ ከእጁ ወልቃ ትጠፋለች። አምባሯ እንደ መኪና ጎማ እየተሽከረከረች ከልዑሉ ዓይን ትሰወራለች።
ቢያስስ ቢያስስ የአንባሯን አድራሻ ሊያገኝ ያልቻለው ልዑሉ ከሥፍራው የሚገኝ ጉብታ ላይ ወጥቶ በዓይኑ ሲያማትር አምባሯ ስታበለጨልጭ ያያታል። ወርዶ እቦታው ላይ ሲደርስ ግን አምባሯ የውሃ ሽታ ትሆነበታለች።
መልሶ ወደ ጉብታው ሲወጣ፤ ሲወርድ ውሎ ተስፋ ሲቆርጥ ከአውራሪስ ቀንድ በተሠራው ጥሩንባ መሬቱን እየወጋ ምድሪቱን ይረግማታል። እንዲህ በማለት «አንቺ ምድር የተረገምሽ ሁኚ፤ ምስቅልቅልሽ ይውጣ»
ከዚያን ቀን ጀምሮ ሜዳ የነበረው ቦታ እየተሰነጠቀ የአሁኑን 'ኒው ዮርክ' መሠረተ። ይህ እንግዲህ የገሰረጆ ቀበሌ የዕድሜ ባለፀጋዎች ከሆኑት አንዱ አቶ አዱላ አሰፋ የሚሉት ነው። «አያቶቻችን ለአባቶቻችን ነገሯቸው፤ አባቶቻችን ደግሞ ለእኛ፤ እኛ ደግሞ ይኸው ለልጆቻችን. . .»

ጤሃጣ
ከአሸዋማ አፈር ተጠቅጥቀው የተሠሩ ተፈጥሯዊ ሕንፃዎች። ቢነኳቸው ፍርክስክስ የሚሉ የሚመስሉ ነገር ግን ዘመናትን የተሻገሩ መልክዓ-ምድራዊ ስጦታዎች።
ይህ ተፈጥሯዊ መልክዓ ምድር የሚገኝበት ሥፍራ ገሰረጆ ቀበሌ ይባላል። በተለምዶ ኒው ዮርክ የሚባለው ሥፍራ ደግሞ ጤሃጣ [ኮንሶዎች ሲጠሩት ምላሳቸውን ከላይኛው ላንቃ ጋር አጣብቀው ነው] ይሉታል።
እና 'ኒው ዮርክ' የሚለው ስም ከየት መጣ?
«እኛ ጤሃጣ እንለዋለን እንጂ ኒው ዮርክ የሚለውን ስያሜ የሰጡት ፈረንጆች ናቸው። ልክ እንደቤት መስኮት እና በር ያላቸው ዋሻዎች አሉት። ይህንን ያዩ ፈረንጆች እኛ ሃገር ያለውን ኒው ዮርክ ይመስላል ብለው በዚያ ሰየሙት።»
የጤሃጣ አሸዋማ ሕንፃዎች ዓይነ-ግቡ ናቸው። ሲያይዋቸው የእንቧይ ክምር ነው የሚመስሉት። በስንጥር ቢጤ ነካ ቢያደርጓቸው ፍርስርስ የሚሉ ይመስላሉ። ግን ይኸው ዝናብ ፀሐይን ተቋቁመው ዘመናትን ዘልቀዋል።
የገሰርጆ ሕፃናት እንደ ጦጣ ሲንጠላጠሉባቸው ማዬት ከአሁን አሁን ወደቁ በሚል ሰቀቀን ውስጥ ቢከትም እነርሱ ተክነውበታል። ከአለት የጠነከረ የአሸዋ ክምር መሆኑንም ያውቁታል።
«እኔ ስወለድም እንደዚህ ነበር፤ ሳድግም ምንም ዓይነት ለውጥ አላሳየም፤ ይኸውም አርጅቼም ያው ነው» ይላሉ ሽማግሌው አቶ አዱላ።
ኋይት ሃውስ፣ ፔንታጎን፣ ላሊበላ እኚህ ስሞች በኒው ዮርክ የተለመዱ ናቸው። ጎብኚዎች የሕንፃ ቅርፅ ያላቸው እኒህን የአሸዋ ክምሮችን ሲያዩ 'ይህማ ላሊባላን ይመስላል'፤ ይህኛው ደግሞ ፔንታጎንን በማለት ስያሜ ይሰጧቸዋል።
የኮንሶ ጤሃጣ ወደታች እስከ 80 ሜትር ድረስ ይጠልቃሉ።

ኮንሶን በሥራም ይሁን ለጉብኝት የረገጠ ተጓዥ ይህን አስደናቂ ቦታ ሳይመለከትና በተፈጥሮ ጥበብ ሳይደነቅ ቢመጣ እውነት ይቆጨዋል። አሁን አሁን የጎብኚ ቁጥር በተነፃፃሪ ቢቀንስም የውጭ እና የሃገር ውስጥ ጎብኚዎች ወደ ጤሃጣ [ኒው ዮርክ] መፍሰሳቸው አልተገታም። ከአርባምንጭ ኮንሶ ያለው መንገድ ባብዛኛው ጥርጊያ በመሆኑ ምቾት መንሳቱ አይቀርም።
የሥነ-ምድር ተመራማሪዎች እንደ ኒው ዮርክ ያሉ ተፈጥሮዎችን 'ካንየን' ወይም 'ጎርጅ' ይሏቸዋል። እኒህ የተፈጥሮ ትሩፋቶች በሁለት ዓይነት መንገድ እንደሚፈጠሩ ነው ሳይንሱ የሚያስረዳው።
አንደኛው የመሰል ተፈጥሯዊ ክስተቶች መንስዔ ከባድ ዝናብ የሚያስከትለው የመሬት መሸርሸር ነው። ሌላኛው ደግሞ ዝናቡ ያስከተለው ጎርፍ ወይም ወንዝ ጎርጆችን [ካንየን] በሁለት የመክፈሉ ነው። በዓለም ላይ ከሚታወቁ በርካታ 'ካንየኖች' አብዛኛዎቹ በመሃላቸው ወንዝ ይፈሳል።
ኒው ዮርክ ወይም ጤሃጣ ግን ወንዝም አይፈስበትም፤ ዝንብም ሆነ ጎርፍ አልበገረውም [ቢያንስ በእኛ ዘመን]። ግን እንክብካቤና ጥበቃን ይፈልጋል።












