በህንድ ከመደፈር ለመዳን የታገሉትን ሴቶች ፀገራቸውን በመላጨት ያሸማቀቁት ታሰሩ

በህንድ ራሳቸውን ከመደፈር የታገሉትን ሴቶች ፀገራቸውን በመላጨት ያሸማቀቁት ታሰሩ

የፎቶው ባለመብት, ANI

በህንድ ባህር ግዛት ቁጥሩ ያልተገለፀ የወንዶች ስብስብ ሁለት ሴቶችን ሊደፍሩ ሞክረው ሴቶቹ ራሳቸውን ለመከላከል በመታገላቸው በምላሹም ለቅጣት ብለው ፀጉራቸውን ላጭተዋቸዋል።

የአካባቢውን ባለስልጣን ያካተተው ይህ ቡድን አንዲት እናትና ልጇን ቤታቸው በመሄድ ለመድፈር ሙከራ ማድረጋቸውን ፖሊስ የገለፀ ሲሆን ከዚህም ጋር በተያያዘ እስካሁን ሁለት ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለዋል።

ሴቶቹም ራሳቸውን ለማዳን የታገሉ ሲሆን በምላሹም ቡድኑ ደብድበው ፣ ፀጉራቸውን ላጭተው በመንደሩ ውስጥ እያዘዋወሩ መተዛዘቢያ እንዳደረጓቸው ተገልጿል።

በዚህ ተግባር ላይ የተሳተፉትን ሌሎች አምስት ግለሰቦችንም ፖሊስ እየፈለገ እንደሆነ ገልጿል።

"በዱላ በከፍተኛ ሁኔታ ተደብድበናል፤ ሰውነቴ ቆሳስሏል የልጄም እንዲሁ" በማለት እናቷ ኤኤንአይ ለተባለው የዜና ወኪል ተናግራለች።

ሴቶቹ እንደተናገሩት ፀጉራቸውንም የላጯቸው የመንደሩ ሰዎች በተሰበሰቡበት ነው።

Presentational grey line

'ህግን አይፈሩም'

ጌታ ፓንዴይ፣ ቢቢሲ ኒውስ ከዴልሂ

የመድፈር ሙከራው ወንጀል ነው፤ ተከትሎም የተከሰተው ፀጉራቸውን ላጭቶ በመንደሩ ማዘዋወር ወንዶች በማህበሩ ውስጥ ያላቸውን የኃይል ሚዛን መግለጫ መንገድ ነው፤ ይህም በማህበረሰባችን ውስጥ ባለው የአባታዊ ስርዓት (ፓትሪያርኪ) ውስጥ ስር ሰዶ የሚገኝ ነው።

ከሁሉም በላይ ደግሞ ጉዳዩን አሳሳቢ የሚያደርገው ህዝቡ የኔን ደህንነት ያስጠብቅልኛል፤ እንዲሁም ይወክለኛል ብሎ የመረጠው የመንግሥት ባለስልጣን በጉዳዩ ላይ መሳተፉ ነው።

የተፈፀመውም ወንጀል በህንድ ውስጥ ግለሰቦች ህግን እንደማይፈሩ ማሳያ ነው።

ሲጀመር ደሃና ከኢኮኖሚው የተገለለው ማህበረሰብ ምንም አይነት ወንጀል ቢፈፀምባቸው ለፖሊስ ለመንገር ይፈራሉ። ድንገት እንኳን ጉዳዩ ፖሊስ ጋር ቢደርስም ምርመራው ትኩረት ሳይሰጠው አንዳንዴ በዘፈቀደ ስለሚታለፍ ባለስልጣናትና ኃይል ያላቸው ግለሰቦችም ሰው ገድለውም ቢሆን ማምለጥ ይችላሉ።

ምንም እንኳን እንዲህ አይነት ወንጀሎች ሲፈፀሙ የህዝቡ ቁጣ ከፍተኛ ቢሆንም ይህ ግን የሚዘልቀው ለአጭር ጊዜ ነው።

Presentational grey line

የግዛቱ የሴቶች ኮሚሽን በበኩሉ ጉዳዩን ካወገዙ በኋላ ጥቃቱን ያደረሱት ለፍርድ እንደሚቀርቡ ቃል ገብተዋል።

በግዛቱ እንዲህ አይነት ጥቃት ሲደርስ የመጀመሪያው አይደለም፤ በሚያዝያ ወር ላይም በደቦ ልትደፈር የነበረች ልጅ ራሷን ከጥቃት ለመከላከል በመታገሏ አሲድ ተደፍቶባታል።

ከዚህ በተጨማሪ ከጥቂት ወራት በፊት አንዲት ሴትንም እንዲሁ ልብሷን አስወልቀው ራቁቷን በመንደሩ ውስጥ በማዘዋወር መታዛዘቢያ እንዳደረጓትም እንዲሁ ተዘግቧል።

ከሰባት አመታት በፊት አንዲት ተማሪ በአውቶብስ ውስጥ በደቦ ተደፍራ መገደሏን ተከትሎ ከፍተኛ የህዝብ ቁጣ መቀስቀሱ የሚታወስ ነው።

ከዚያም በኋላ በባለፈው አመትም ከፍተኛ ባለስልጣናት በህፃናት መድፈር ወንጀል እጃቸው አለበት መባሉንም ተከትሎ ቁጣው አገርሽቷል።

ነገር ግን አሁንም ቢሆን በሴቶች ላይ የሚፈፀሙ የመድፈር ወንጀሎችና ጥቃቶች እንደተበራከቱ ሪፖርቶች ያሳያሉ።