በኢትዮጵያ ብዙ ቦታዎች ተቋርጦ የነበረው የኢንተርኔት አገልግሎት ተመለሰ

የኔትብሎክስ መረጃ

የፎቶው ባለመብት, Netblocks

የምስሉ መግለጫ, የኔትብሎክስ መረጃ

ዛሬ ከጠዋቱ አንድ ሰዓት ተኩል ጀምሮ በበርካታ የኢትዮጵያ ክፍሎች የኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጡን ኢትዮ ቴሌኮም ለቢቢሲ ያረጋገጠ ሲሆን፤ አገልግሎቱ ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት ተመልሷል።

በአገሪቱ ብቸኛ የኢንተርኔት አገልግሎት አቅራቢ የሆነው የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጽህፈት ቤት ኃላፊ የሆኑት ወ/ት ጨረር ኢንተርኔት ተቋርጦ እንደነበር ለቢቢሲአረጋግጠዋል።

ወ/ት ጨረር ለኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጡ ምክንያት ምን እንደሆነ አልተናገሩም።

የመረጃ መረብ ደኅንነትንና በዓለም ዙሪያ የኢንተርኔት ስርጭትን የሚከታተለው ኔትብሎክስ የተሰኘው መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት በአገሪቱ ሙሉ በሙሉ የኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጡን በትዊተር ገፁ ላይ አስፍሮ ነበር።

ለዚህም እንደ ምክንያትም የጠቀሰው በትናንትናው ዕለት በመላው አገሪቱ የተጀመረው አገር አቀፍ ፈተና ላይ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ማጭበርበሮችን ለመከላከል እንደሆነ ነው።

የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገፅ የኢንተርኔት ትራፊክ መቆጣጠሪያ ከዛሬ ጥዋት ጀምሮ እንዳመለከተው፤ ከኢትዮጵያ ድረ ገፁን የሚጎበኙ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሷል።

ከሁለት ዓመታት በፊት የብሔራዊ ፈተና ስርቆትን ለመከላከል በሚል በፈተናው ወቅት የኢንትርኔት አገልግሎት እንዲቋረጥ ተደርጎ እንደነበር ይታወሳል።

እስካሁን የኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጡን በተመለከተ ከመንግሥትም ሆነ ከሚመለከተው አካል የተሰጠ ማብራሪያ የለም።