ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ፍርድ ቤት፡ ኤል ቻፖ ከእስር ክፍሉ ለአካላዊ እንቅስቃሴ መውጣት ተከለከለ
''ኤል ቻፖ'' በሳምንት ለሁለት ሰዓታት ከእስር ክፍሉ ውጪ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን ለማድረግ ያቀረበውን ጥያቄ የኒውዮርክ ዳኛ ውድቅ አደረጉ።
ዳኛው ኤል ቻፖ ይህን ምክንያት ያመጣው ከእስር ለማምለጥ አስቦ ነው ሲሉ ተከራክረዋል።
ዮአኪን ጉዝማን ወይም ኤል ቻፖ ተብሎ የሚጠራው ሜክሲኳዊው የዕፅ ነጋዴ ከአንድም ሁለቴ ከፍተኛ ጥበቃ ከሚደረግላቸው የሜክሲኮ እስር ቤቶች በተለያዩ ጥበቦች ከእስር ማምለጥ ችሏል።
ከወራት በፊት በዕፅ ዝውውር ወንጀለኛ የተባለ ሲሆን ከ20 ቀናት በኋላ ፍርድ ይተላለፍበታል።
የ61 ዓመቱ ኤል ቻፖ በህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ባለቤትነት እና በህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውርም ክሶች ቀርበውበታል።
የፍርድ ውሳኔውን የሚጠባበቀው ኤል ቻፖ የተቀረውን እድሜውን በእስር ሊያሳልፍ እንደሚችል ተገምቷል።
ሲቢኤስ ኒውስ እንደዘገበው ኤል ቻፖ የጥፋተኝነት ውሳኔ የተላለፈበት ቀን ምንም አይነት የስሜት መለዋወጥ አላሳየም ነበር።
ዮአኪን ጉዝማን ኒው ዮርክ ማንሃተን በሚገኝ እስር ቤት ውስጥ ያለ ሲሆን፤ ጠበቃዎቹ ኤል ቻፖ የተያዘበት ሁኔታ ''ተፈጥሯዊ ያልሆነ እና ሰብዓዊነት የጎደለው ነው'' ሲሉ ገልጸውታል። ጠበቆቹ እንደሚሉት ቻፖ አካላዊ እንቅስቃሴ እንዲያደርግ የሚፈቀድለት በሳምንት አንድ ቀን ብቻ የእስር ቤት ክፍል ውስጥ ነው።
የቻፖ ጠበቃ ለፍርድ ቤቱ ባቀረበችው ጽሁፍ ደንበኛዋ ንጹህ አየር እና የጸሃይ ብርሃን ካየ ሁለት ዓመታት እንደተቆጠሩ አስረድታለች። ጠበቃዋ እንደምትለው ከሆነ ዮአኪን ጉዝማን ወደ አሜሪካ ተላልፎ ከተሰጠ ወዲህ ወደ ፍርድ ቤት ሲሄድ ብቻ ካልሆነ በቀር የጸሃይ ብርሃን አይቶ አያውቅም።
አቃቤ ሕግ ግን በእስር ቤቱ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ የሚቻለው የእስር ቤቱ ጣሪያ ላይ ብቻ ነው ብሏል።
''ፍርደኛው (ኤል ቻፖ) ከዚህ ቀደም ከፍተኛ ጥበቃ ከሚደረግላቸው ሁለት እስር ቤቶች ማምለጥ ችሏል። መብራት የተገጠመለት፣ ንጹህ አየር የሚነፍስበት እና 1.6 ኪ.ሜ የሚረዝም ዋሻ አስቆፍሮ ያመለጠ ፍርደኛ፤ ከእስር ቤቱ አናት ላይ በሄሊኮፍተር ወይም በሌላ መንገድ ማምለጥ ለእርሱ ተራ ነገር ነው።'' በማለት ባለስልጣናት የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ደግፈዋል።
በተያያዘም፤ የዮአኪን ጉዝማን እናት የሆኑት የ91 ዓመቷ ማሪያ ኮንሱኤሎ በአሜሪካ እስር ላይ የሚገኘውን ልጃቸውን ለመጎብኘት ከአሜሪካ መንግሥት ፍቃድ ማግኘታቸውን አስታቀዋል።
ጉዝማን ለእናቱ ከፍተኛ ፍቅር እንዳለው ይነገራል።
ኤል ቻፖ ጉዝማን ማነው?
"ኤል ቻፖ'' ማለት ''አጭሩ'' እንደማለት ሲሆን በሰሜናዊ ሜክሲኮ ሲናሎአ የተሰኘ የዕፅ አዘዋዋሪ ቡድን መሪ ነበረ።
ኤል ቻፖ የሚመራው ቡድን ወደ አሜሪካ ለሚላከው ዕፅ ትልቁን ድርሻ ይዞ ነበር። እ.አ.አ. 2009 ፎርብስ ኤል ቻፖ ጉዝማን የተጣራ 1ቢሊዮን ዶላር ያስመዘገበ ከበርቴ ነው በማለት የዓለማችን 701ኛው ሃብታም ሲል የከበርቴዎች ዝርዝር ውስጥ አካቶታል።
ጉዝማን ለቀድሞው የሜክሲኮ ርዕሰ ብሔር ኤንሪክ ፔና ኒቶ በ2012 ስልጣን ከያዙ በኋላ እርሱ ላይ የሚደረገው ክትትል እንዲቆም በመጠየቅ አንድ መቶ ሚሊየን ዶላር ጉቦ መክፈሉም የተሰማው ችሎት ላይ ነበር።
ርዕሰ ብሔሩ ግን ይህ ውንጀላ እውነትነት የለውም ሲሉ አስተባብለዋል።
ገድሎ ያቃጠላቸው የአደንዛዥ ዕፅ ከበርቴ ተፎካካሪዎች እንዳሉ ከዘመዶቹ መካከልም የገደላቸው እንዳሉ ተገምቷል።
ችሎቱ ኤል ቻፖ በ2015 በሜክሲኮ እጅግ ጥብቅ ከሆነው እስር ቤት እንዴት እንዳመለጠም በዝርዝር አድምጧል። ልጁ በእስር ቤቱ አቅራቢያ የሚገኝ ቤት እንደተከራየና ጂፒኤስ ያለው ሰዓት ወደ እስር ቤቱ በድብቅ ማስገባቱ ተመስክሯል።
በሚስቱ እና በቅምጦቹ ላይ ለመሰለል በስልኩ ላይ ሶፍትዌር ይጠቀም እንደነበርም ተመስክሮ፤ ኤፍ ቢ አይ የተለዋወጣቸውን የፅሑፍ መልዕክቶች እንዲያቀርብ ተደርጓል።
በአንድ የፅሁፍ መልዕክቱ ላይም ከነበረበት ቤት አሜሪካዊያንና ሜክሲኳዊያን ከከፈቱበት ድንገተኛ ዘመቻ እንዴት እንዳመለጠ የሚገልጽና ልብስ፣ ጫማ እንዲሁም ጥቁር ሸሚዝ እንዲመጣለት የጠየቀበት መልዕክቱም ተነቧል።
ጉዝማን በአሜሪካ የፍትህ አደባባይ ለፍርድ ከቀረቡ የሜክሲኮ የአደንዛዥ ዕፅ ከበርቴዎች መካከል ትልቁ ነው።