ታዋቂው ኬንያዊ ደራሲ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ

ቢንያቫንጋ ዋይኒያና

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ቢንያቫንጋ ዋይኒያና

እውቁ ኬኒያዊ ደራሲ ቢንያቫንጋ ዋይኒያና በ48 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት መለየቱን ቤተሰበቦቹ አረጋገጡ።

ደራሲው በ2002 የኬን ተሸላሚ የነበረ ሲሆን በ2014 ደግሞ ታይም መፅሔት ከዓለማችን 100 ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች መካከል አንዱ አድርጎ አካትቶት ነበር።

ቢንያቫንጋ ዋይኒያና በዓለም ዙሪያ በተለይ የሚታወቀው 'ሃው ቱ ራይት አባውት አፍሪካ' በተሰኘው ምጸታዊ መጣጥፉ ነው።

ቢንያቫንጋ ዋይኒያና በኬንያ በይፋ ተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪ መሆኑን የተናገረ የመጀመሪያው ታዋቂ ግለሰብ ነው፤ ባለፈው ዓመትም ጋብቻ ሊፈጽም መሆኑን አሳውቆ ነበር። በዚህም የተመሳሳይ ፆታ ጋብቻ ሕገ ወጥ በሆነባት ኬንያ የተለያዩ ሃሳቦች ተንጸባርቀው ነበረ።

ቢንያቫንጋ ዋይኒያና ከአራት ዓመታት በፊት በጽኑ ታሞ እንደነበረ ተናግሯል።

የማረፉ ዜና ከተሰማ በኋላ ወንድሙ ለቢቢሲ እንደተናገረው፤ ቤተሰቡ የቢንያቫንጋ ዋይኒያና በሕይወት የቆየበትን የስኬት ዘመን እንደሚዘክሩ ተናግሯል።

ዋይኒያና የተመሳሳይ ፆታ ግንኙነት መብት ተከራካሪ በመሆን የሚታወቅ ሲሆን፤ በተለያዩ ጆርናሎች ላይ ባሳተማቸው ጥናታዊ ሥራዎቹ፣ በረዥምና አጫጭር ልቦለድ ድርሰቶቹ ይታወሳል።