በአሜሪካ በእርሻ መሣሪያ የተያዘው አርሶ አደር እግሩን ቆረጠ

የእርሻ መሣሪያ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, መሣሪያው አንደ መብሻ (ድሪል) የሚሽከረከር ነው።

በአሜሪካ ኔብራስካ ግዛት በእርሻ ሥራ ላይ ሳለ ሰብል መሰብሰቢያ መሣሪያ ውስጥ እግሩ የተቀረቀረበት አርሶ አደር በስለት የራሱን እግር ቆርጦታል።

የ63 ዓመቱ አርሶ አደር ኩርት ካሴር ምርት ለመሰብሰብ የሚረዳውን ማሽን ከአንድ ቦታ ወደ አንድ ቦታ እያዘዋወረ ነበር፤ ማሽኑ ልክ እንደ መብሻ (ድሪል) ዓይነት ሲሆን የሚሽከረከርም ነው።

ግለሰቡ የግሉ በሆነው 607 ሔክታር መሬት ላይ ብቻውን እየሰራ ሳለ ነበር አደጋው ያጋጠመው። በአቅራቢያው ሰዎች ባለመኖራቸው የሚረዳው አላገኘም። ስልክ በመደወል የሰዎችን እርዳታ ለመጠየቅ ቢያስብም ተንቀሳቃሽ ስልኩን አጠገቡ ሊያገኘው አልቻለም።

ማሽኑ እግሩን እየከረከረ የበለጠ ወደ ውስጥ እየዘለቀና ከፍ እያለ መጣ።

በዚህ ጊዜ ደፋሩ ገበሬ የያዘውን ስለት ሳብ አድርጎ ከማሽኑ የተረፈውንና ከጉልበቱ በታች ያለው የራሱ እግር ላይ እርምጃ ወሰደ።

የ X ይዘትን ይለፉት
ይዘቱን X ይፈቅዳሉ?

ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።

ማሳሰቢያ፡ የሦስተኛ ወገን ይዘቶች ማስታወቂያ ሊኖራቸው ይችላል

የ X ይዘት መጨረሻ

መጥፎ አጋጣሚውን ሲያስታውስም "ራሴን ለማላቀቅ ጣርኩ፤ ነገር ግን አጥንቴ ተጣብቆ ቀረ" ሲል ለኦማሃ ወርልድ ሄራልድ ተናግሯል።

"ምንም ምርጫ አልነበረኝም" የሚለው አርሶ አደሩ ከታችኛው የእግሩ ክፍል 7.6 ሴንቲ ሜትር (3 ኢንች) የሚሆነውን የራሱን እግር ቆርጦ ጥሎታል።

ከዚህ ሁኔታ ከተላቀቀ በኋላ ነበር ስልኩን ወደ አስቀመጠበትና 100 ሜትር ወደ ሚርቀው ቦታ እየተንፏቀቀ ሄዶ ለልጁ የደወለለት።

ከዚያም በሊንኮልን ከተማ በሚገኝ የህክምና ተቋም እርዳታ ሲደረግለት ቆይቷል፤ ከጉዳቱ ለማገገምም ሳምንታትን በሆስፒታል አሳልፏል።

ግለሰቡ ለኤቢሲ ኒውስ በማሽኑ ላይ የተገጠመውን መከላከያ አውልቆት እንደነበር ተናግሯል። "ያንን ነገር ሳላስተካክለው በመቅረቴ በራሴ በጣም ነው የተበሳጨሁት" ብሏል በቁጭት።