የሲሪ ላንካ ጥቃት፡ የዋናው ተጠርጣሪ ቤተሰቦች ተገደሉ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ከሳምንት በፊት የፋሲካ በዓል በተከበረበት ወቅት በሲሪላንካ የደረሰው ጥቃት ተጠርጣሪ ዛህራን ሀሺም አባትና ሁለት ወንድሞቹ ባለፈው አርብ በፀጥታ ኃይሎች መገደላቸውን ፖሊስ አስታወቀ።
ሀሺም አሁን የታገደውንና ኤን ቲ ጀ የተሰኘ እስላማዊ ቡድን የመሰረተ ሲሆን ኮሎምቦ በሚገኝ ሆቴል ራሱ ላይ ቦምብ በማጥመድ አፈንድቷል።
ታዲያ ባለፈው አርብ የፀጥታ ኃይሎች በሀሺም መኖሪያ ካታንኩዲ አቅራቢያ የሚገኘው ሴንታማሩትን ተቆጣጥረው ነበር። ከዚያም ወደ ውስጥ ዘልቀው ሲገቡ የታጠቁ ሰዎች ተኩስ ከፈቱባቸው።
ሶስት ወንዶች ፍንዳታ ፈፅመው ራሳቸውን አጠፉ። በዚህም ስድስት ህፃናትና ሶስት ሴቶች ሕይወት ተቀጠፈ።
ቀሪዎቹ አራቱ ደግሞ በተኩስ ልውውጡ ሕይወታቸው አልፏል። የሀሺም የቅርብ ዘመድ ለቢቢሲ እንደገለፀው በተኩሱ የሀሺም አባትና ሁለት ወንድሞቹ ተገድለዋል።
የፖሊስ ምንጭ ለሮይተርስ የዜና ወኪል እንዳስታወቀው ሞሃመድ ሃሺም እና ልጆቹ ዜኔ ሀሺም እና ሪልዋን ሀሽም ተገድለዋል ብሏል።
የዛህራ ሀሺም እናት ከሟቾቹ መካከል ሳይሆኑ እንዳልቀረ ፖሊስ ገልጿል።
አሁንም የፀጥታ ኃይሎች በአገሪቱ አሰሳ እያደረጉ ሲሆን የአካባቢው ነዋሪዎች ለፖሊስ በሰጡት ጥቆማ እና ጥርጣሬ ቢሰጣቸውም፤ ይህንን ቤት ያገኙት ግን እንደ ዕድል ነው ተብሏል።
በእያንዳንዱ ቀን ፖሊስ ሰዎችን ያስራል፤ የጦር መሳሪያዎችን ይይዛል።
አሁን እየተደረገ ያለው ድንገተኛ ፍተሻና የመሳሪያዎች መያዝ ታዲያ በማህበረሰቡ ዘንድ ቀስ በቀስ ስጋት እየፈጠረ እንደሆነም ተነግሯል። አንድ የሆቴል ባለቤት እንዳለችው የካቶሊክ እምነት ተከታይ በመሆኗ ስጋት እንደገባት ገልፃለች። ሙስሊሞች በበኩላቸው በርካታ ሰዎች የሚኖሩበትን ሲንሃላ ለመጎብኘት እንደሚፈሩ ተናግረዋል።
አንዳንድ የውጭ ድርጅቶችም ሌላ ጥቃት ሊፈፀም ይችላል ሲሉ ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል።
ባለፈው ሰኞም ሙስሊም ሴቶች ፊታቸውን እንዳይሸፍኑ የሚለው ህግ ከወጣ አንስቶ ፕሬዚደንት ማትሪፓላ ሲሪስና የአገሪቱን ፀጥታ ለማስከበር የወሰዱት አስቸኳይ እርምጃ እንደሆነ አስታውቀዋል።
ማሳሰቢያው በተለየ ሁኔታ ዐይንን ብቻ የሚያሳይ አስላማዊ አለበበስ (ዐይነ እርግብ) ወይም አይንን ሙሉ በሙሉ የሚከልለውን (ቡርካ) ብሎ የማይጠቅስ ቢሆንም ሰዎች በቀላሉ ማንነታቸው እንዲታይ ፊታቸው ሙሉ በሙሉ መታየት አለበት ብለዋል።
በአገሪቱ እሁድ ዕለት የሚሰጡ የቤተ ክርስቲያን አገልግሎቶች ተሰርዘዋል። ይሁን እንጂ ፀሎትና ሌሎች ስነ ስርዓቶች ጥቃት ከተፈፀመበት ከቅዱስ አንቶኒ ቤተክርስታያን አቅራቢያ ተከናውኗል።
ባለፈው እሁድ ለፋሲካ በዓል ለፀሎት የተሰባሰቡ ሰዎች በሞሉበት ቤተክርስቲያን ላይ በደረሰው ጥቃት ከ 250 በላይ ሰዎች የሞቱ ሲሆን 500 ሰዎች ለጉዳት ተዳርገዋል።
ከሟቾቹ አብዛኞቹ ሲሪ ላንካውያን ሲሆኑ ሌሎች የውጭ ዜጎችም ይገኙበታል።
የአገሪቱ ባለስልጣናት እንዳስታወቁት ለጥቃቱ ኤን ቲ ጀን ተጠያቂ ያደረገ ሲሆን ጠንካራ በሆነ ኔትወርክ ሳይደገፉ እንዳልቀረም አስታውቀዋል።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በፓሪስና በተለያዩ ቦታዎች ጥቃት ያደረሰው እስላማዊ ታጣቂ ቡድን ( አይ ኤስ) እጁ ሳይኖርበት አይቀርም ተብሏል። ይሁን እንጂ ዝርዝር መረጃ አላቀረበም ።












