የፈረሰው የደጃዝማች ዐምዴ አበራ ቤት ጠባቂ ምን ይላል?

የፎቶው ባለመብት, Setse Firesbhat
መጋቢት 17/2011 ዓ.ም በአዲስ አበባ የካ ክፍለ ከተማ በቅርስነት ተመዝግቦ የነበረው የደጃዝማች ዐምዴ አበራ መኖሪያ ቤት ከቤቶች ኮርፖሬሽን ታዘን ነው በሚሉ ሰዎች መፍረሱን የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሐን ዘግበዋል። ድርጊቱ በቤቶች ኮርፖሬሽን፣ በቅርስ ጥበቃ፣ በክፍለ ከተማ እንዲሁም በባህል፣ ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ መካከል ውዝግብ የፈጠረ ነው።
መረጃዎች እንደሚያሳዩት የደጃዝማች ዐምዴ አበራ መኖሪያ ቤት በ1967 ዓ.ም በደርግ ከተወረሰ በኋላ በኪራይ ቤቶች አስተዳደር ስር ሆኖ ግለሰቦች በኪራይ ኖረውበታል። ከ1977 ዓ.ም ጀምሮ ሕይወታቸው እስካለፈበት 2002 ዓ.ም ድረስ ከቤተሰቦቻቸው ጋር የኖሩበት ጁሴፔ የተባሉ ጣሊያናዊ ናቸው።
ኃይለእየሱስ በክሩ በአጋጣሚ ትውውቅ ከጣሊያናዊው ጋር አንደ አንድ የቤተሰብ አካል ሆኖ ይኖር ነበር።
ትውውቁ የጀመረው ጣሊያናዊው ከባለቤቱ ጋር በፍች ተለያይተው ስለነበር በዚሁ ቤት ውስጥ በወር 300 ብር ለኪራይ ቤቶች እየከፈሉ ሁለት ልጆቻቸውን በሞግዚት ያሳድጉ ነበር።
የእርሳቸው ልጅ ኤርኔስቶ ኮዜንቲኖ ከኃይለእየሱስ ጋር የአንድ ሠፈር ልጅ በመሆኑ አብረው ኳስ ይጫወታሉ። እርሳቸውም ቢሆን በአካባቢው የእግር ጉዞ ማድረግን ያዘወትሩ ነበር።
በዚህ መካከል ጣሊያናዊው ቤቱን በሚጠብቁላቸው ግለሰቦች እንደተማረሩ የልባቸውን ያጫውቱታል። ለጨዋታ ብቻም ሳይሆን ጭንቀታቸውን እንዲጋራ አስበው ነበርና ከእርሳቸው ጋር እየኖረ ቤቱን እንዲጠብቅ ይጠይቁታል። ኃይለእየሱስ ጥያቄያቸው አይኑን ሳያሽ ተቀበለ።
በአባትና ልጅ ግንኙነት ሥራውን ጀመረ -ኃይለየሱስ። በዚህ መካከል "እንደ ልጃቸው አሳድገውኛል" የሚላቸው ጣሊያናዊ በልብ ሕመም ምክንያት በድንገት በሞት ተለዩ።
"የጁሴፔ ባለቤት ወደ አገር ውስጥ መጥታ ንብረቶቹን ወሰደች፤ ቤቱን እንድጠብቅና እንድንከባከብ የኪራይ ቤቶች አስተዳደር ቁልፍ ሰጠኝ" የሚለው ኃይለእየሱስ በዚህ መልኩ ቤቱን እየጠበቀ ለ6 ዓመታት እዚያው ግቢ ውስጥ አትክልቶቹን እየተንከባከበና ቤቱን እየጠበቀ ኖረ።
ይሁን እንጅ ከአራት ወራት በፊት ቤቱን ለቆ እንዲወጣ መጠየቁን ያስታውሳል። በብዙ ሙግት ከቆየ በኋላ ቤቱን በለቀቀ ማግስት መጋቢት 17/2011ዓ. ም ቤቱን ፈርሶ እንዳገኘው ይናገራል።

የፎቶው ባለመብት, Yeka Communication Affairs Office FB
"ከውስጤ አንድ ነገር እንዳጣሁ ነው የተሰማኝ፤ በማልቀስ ነው የገለፅኩት... ለማየት እንኳን የሚሳሳለት ቤት በዚህ መልኩ መፍረሱ ከልቤ አሳዝኖኛል" ሲል ይገልፃል። ቤቱ ታድሶ ተጠብቆ ይኖራል የሚል እንጂ ይፈርሳል የሚል ቅንጣት ያህል ስጋት እንዳልነበረውም ይናገራል።
የደጃዝማች ዐምዴ አበራ መኖሪያ ቤት የቀደመውን ዘመናዊ የቤት አሰራርን የሚገልጥ ጥበብ ያለው ነው የሚለው ኃይለየሱስ ወለሉ በጣውላ፤ የጭስ ማውጫው በእብነ በረድ የተሰራ ሲሆን በቤቱ ውስጥ የተለያዩ ቅርፃ ቅርፆችም ነበሩ። "የጣሪያው ዲዛይን በጣም የተለየ ነው፤ በዘመናዊ ጣውላ የተሰራ ነው፤ አሰራሩ በቃ ለየት ያለ ነው" ይላል።
በግቢው ውስጥ የዋናውን ቤት ያህል አሰራራቸው የተለየ ባይሆኑም 6 ክፍል ቤቶች የነበሩ ሲሆን፤ ከዚህ ቀደም እንዲፈርሱ እንደተደረገ ያስታውሳል። ከዚህ በተጨማሪም ዓይነተ ብዙ የሆኑ እንደ የሀበሻ ፅድ፣ ወይራና ሌሎች እድሜ ጠገብ ዛፎች ይገኙበታል።
"በመኪና ተገጭቶ ፈርሶ ነው እንጂ 'ፋውንቴንም' ነበረው" ይላል።
እርሱ እንደሚለው መኝታ ቤት፣ የእንግዳ ማረፊያ፣ ሳሎንና በረንዳው እንዳሉ ፈርሰዋል፤ የሚታየው ፊት ለፊት ገፅታም ጉዳት ደርሶበታል።
ደጃዝማች ዐምዴ በደርግ የተገደሉ ሲሆን አባታቸው አበራ ካሣ ደግሞ በጣሊያን በግፍ እንደተገደሉ ታሪክ ያስረዳል፤ ራሳቸውን ለሀገራቸው አሳልፈው ሰጥተዋል። ታዲያ በተወረሰው የእርሳቸው ቤት ጣሊያናዊ መኖራቸው ግጥምጥሞሹ ያስገርማል።
እንደው ምን ይሰማቸው ነበር ያልነው ኃይለየሱስ ቤቱ በጣሊያን እጅ እንደተሰራ ከመንገር በዘለለ የነገሩት እንደሌለ ገልፆልናል።
ከአገር ውጭ የሚገኙት የጣሊያናዊው ልጆች ለቤቱ ልዩ ፍቅር እንደነበራቸውና አንድ ቀን ተመልሰው ሊኖሩበት እንደሚፈልጉ ያጫውቱት እንደነበርም ነግሮናል።
ይሄው ታሪካዊ ቤት ለሙዚቃ ክሊፖችና ፊልሞች የቀረፃ ቦታ ያገለግል ነበር።
የአዲስ አበባ ባህል ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ባዬ በበኩላቸው ቤቱ ላይ የተፈጸመውን ነገር አውግዘዋል። "አዲስ አበባን ትዝታና ታሪክ ያሳጣታል፣ የአዲስ አበባ አከታተም እንዴት እንደተጀመረ፣ የከተሜነቱን ሁኔታ የሚያሳይ ሲሆን ሥነ ህንፃን ማጥናት ለሚፈልጉ ትልቅ ጠቀሜታ የነበረው ነው፤ ደጃዝማች ዐምዴ ለሀገራቸው ሲሉ ህይወታቸው ያለፈ ታላቅ ኢትዮጵያዊ ማስታወሻም ነበር" ሲሉ በሆነው ሁሉ ማዘናቸውን ገልፀዋል።
መኖሪያ ቤቱ በ1930 ዓ.ም እንደተሰራና ከቀደምቶቹ የአዲስ አበባ መኖሪያ ቤቶች አንዱ እንደሆነ ይናገራሉ - ኃላፊው።
ከዚህ ቀደም እንደ ሰፈር የሚቆጠሩ በርካታ ቦታዎች ታሪካቸውን ማጣታቸውንም አውስተዋል። የደጃች ውቤ ሰፈርን፣ አራት ኪሎንና መርካቶን በምሳሌነት ይጠቅሳሉ።
ኃላፊው አክለውም የደጅ አዝማች ዐምዴ አበራን ቤት በተመለከተ በህግ መጠየቃቸውን እንደሚቀጥሉ ገልፀው፤ ጥገና እስከሚደረግለት ፍርስራሹ ባለበት ሁኔታ እየተጠበቀ እንደሆነ ነግረውናል።
የጉዛራን ቤተ መንግሥት ጥገና እያስታወሱ ቤቱ በቀላሉ መልሶ መጠገን እንደሚቻል ከባለሙያዎች አስተያየት ማግኘታቸውን ጠቅሰው ሥራውን ለማከናወን ጥናት እየተደረገ እንደሆነ ለቢቢሲ ገልፀዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ 440 ቅርሶች በተለያየ ይዞታ በቅርስነት ተመዝግበው ይገኛሉ።












