መፈናቀል፡ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ የአንድ ዓመት ፈተናዎች አንዱ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ቃለ መሃላ ፈጽመው ስልጣን ከተረከቡ ድፍን አንድ ዓመት ሆናቸው። በዚህ ቆይታቸውም በርካቶች በሃገሪቱ ታይተው የማይታወቁ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ የለውጥ እርምጃዎችን እንደወሰዱ በመጥቀስ አድናቆታቸውን ይገልጹላቸዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የአንድ ዓመት የአስተዳደር ቆይታ ወቅት የተለያዩ ፈታኝ ሁኔታዎች አጋጥመዋል። ከእነዚህም መካከል በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች የተከሰቱት የብሔር ግጭቶችና እነሱንም ተከትሎ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች መፈናቀል መንግሥታቸው ከሚተችበት ምክንያት አንዱ ነው።
በሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ ውስጥ በምትገኘው ቻግኒ ውስጥ ያለው ተፈናቃዮች የሰፈሩበት አካባቢ ከሁለት ወራት በፊት ምንም ነገር ያልነበረበት ክፍት መስክ ነበረ።
ዛሬ ግን በብሔር ግጭት ምክንያት ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተፈናቀሉ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በነጭና አረንጓዴ ድንኳኖች ተጠልለውበታል፤ መስኩን ሸፍነውታል።
በመጠለያው ውስጥ ከሚገኙት ሰዎች መካከል የሁለት ልጆች እናት የሆነችው የ32 ዓመቷ ፍቅሬ አሳዬ አንዷ ናት። ፍቅሬ ትኖርበት የነበረውን ቀዬዋን ጥላ የሸሸችው ከተቀናቃኝ ጎሳ የመጡ በከፍተኛ ሁኔታ የታጠቁ ቡድኖች ጥቃት አድርሰው በርካቶችን ከገደሉና ካቆሰሉ በኋላ ነበር። ባሏም የት እንደደረሰ አታውቅም።
በመጠለያው ውስጥ ያለውን ሕይወት በተመለከተም ፍቅሬ ስትናገር "እዚህ ከልጆች ጋር መኖር በጣም አስቸጋሪ ነው። በቀያችን በነበርን ጊዜ ለልጆቻችን የሚያስፈልጋቸውን ነገር እናቀርብ ነበር። አሁን ግን ይህን ማድረግ አንችልም፤ በመጠለያው ውስጥ ያለው ሁኔታ በጣም አስከፊ ነው" ትላለች።
ወደ ቀያቸው የመመለሱም ሁኔታ የማይሆን ነገር እንደሆነ የምትናገረው ፍቅሬ "ወደቤታችን መመለስ አንችልም። ሰው እንዴት ብሎ ከወንድሙ ገዳይ ጋር ሊኖር ይችላል?" ስትል ትጠይቃለች።
ነገር ግን በኢትዮጵያ በብሔር ግጭት የተፈናቀሉ ሰዎች የሚገኙት በሰሜን ምዕራቡ የሀገሪቱ ክፍል ብቻ አይደለም።
ከቻግኒ በሺህ ኪሎሞትሮች ርቆ በሚገኘው የደቡባዊ ኢትዮጵያ ክፍልም በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተፈናቅለው በአስቸጋሪ ሁኔታ በጊዜያዊ መጠለያዎች ውስጥ ይገኛሉ። ያለው ሁኔታ እጅግ አስከፊ ሲሆን ባለፉት ስምንት ወራትም ያለበቂ ምግብ፣ መጠለያና የህክምና አገልግሎት በችግር ውስጥ ይገኛሉ።
በኦሮሞዎችና በጌዲዮዎች መካከል ያገረሸውን ግጭት ተከትሎ ከወራት በፊት መኖሪያዋን ጥላ በመሸሽ ላይ እያለች ነበር እቴነሽ አበበ የወለደችው። እሷ እንደምትለው ጨቅላዋ በህይወት በመቆየቷ እድለኛ እንደሆነች ትናገራለች። ምንም እንኳን መንግሥት ደህንነቸውን ለመጠበቅ ቃል ቢገባም እንደሌሎቹ ተፈናቃዮች ወደቀዬዋ ለመመለስ ፈቃደኛ አይደለችም።
ወደመጠለያው ከመጣች በኋላ ልጇ ታማባት እንደነበር የምትናገረው እቴነሽ ያለፈችበትን ችግር ስታስታውስ "ስወልድ የነበርኩበት ሁኔታ በጣም አስቸጋሪ ነበር። ከመጀመሪያው እየተሳደድን ነበር። እኔም በጣም ደም እየፈሰሰኝ ነበር። ባሌ አብሮኝ ስለነበረ ሁለቱን ቀሚሶቼን በመጠቀም ደሙን ለማስቆም እየሞከርን ነበር።"
በኢትዮጵያ ውስጥ ከብሔር ጋር በተያያዙ ግጭቶች ምክንያት ሁለት ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎች ከሚኖሩበት አካባቢ ተፈናቅለዋል። ለግጭቶቹ እንደምክንያት የሚጠቀሱት ለዘመናት የዘለቁ የድንበር ጥያቄዎች፣ በግጦሽ ቦታ ይገባኛልና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ወደስልጣን ከመጡ በኋላ በተከሰቱ ውዝግቦች ነው።
በዚህም ሳቢያ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አስተዳደር በሃገሪቱ የተከሰተውን የተፈናቃዮች ቀውስ የያዘበት ሁኔታ ለከባድ ትችት አጋልጦታል። ይህም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ያጋጠማቸው ትልቁ ፈተና ነው።
የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ መስራችና የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ ኦባንግ ሜቶ በሃገሪቱ ውስጥ እየተከሰተ ስላለው አሳሳቢ ሁኔታ ሲናገር ባለፉት ዓመታት በሃገሪቱ የነበረውን ሁኔታ ይጠቅሳል።
"ሰዎች የሌሎችንን ሰውነት መመልከት እስኪተዉ ድረስ ባለፉት 27 ዓመታት ለሕዝቡ ከኢትዮጵያዊነት ይልቅ ጎሳውን እንዲያስቀድም ነው ሲነገረው የቆየው። ይህ የኢትዮጵያን የአስተሳሰብ ውድቀት ሲሆን ይህንንም ለማስተካከል በጥልቀት ማሰብንና ወደሕዝቡ በመሄድ መነጋገርን ይፈልጋል። እኛን አንድ የሚያደርገን ጎሳችን ሳይሆን ሰው መሆናችን ነው።"
መንግሥት የተፈናቀሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን እንደ አንድ ምክንያት ጠቅሶ በዚህ ወር ማብቂያ ላይ ሊካሄድ ታቅዶ የነበረው የሕዝብ ቆጠራ ለሌላ ጊዜ እንዲተላለፍ አድርጓል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሰነዘረባቸውን ትችት ተከትሎ ለመጀመሪያ ጊዜ በከባድ ችግር ውስጥ ካሉት የተፈናቃይ መጠለያዎች መካል በደቡብ ኢትዮጵያ የሚገኘውን በመጎብኘት ተፈናቃዮቹን ወደቀያቸው እንዲመለሱ እንደሚያደርጉ ቃል ገብተዋል።












