የጉግል አጠቃቀምዎን የሚቀይሩ ሰባት እውነታዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በቀን ውስጥ ጉግልን ምን ያህል ጊዜ ይጠቀማሉ?
ምንም እንኳ ጉግልን አዘውትረው የሚጠቀሙ ቢሆኑም የመፈለጊያ ሳጥኑ ውስጥ የማናውቃቸው ሚስጥራዊ መገልገያዎች አሉት።
ከእነዚህም መካከል ላታውቋቸው ትችላላችሁ ያልናቸውን ነጥቦች እንደሚከተለው አሰቀምጠናቸዋል፤ ይሞክሯቸው።
1.የዕድል ጨዋታ
ሎተሪ መጫዎት ወይም ደግሞ ድንገቴ ውሳኔዎችን መወሰን ያስደስተዎታል? ለዚህ ፍላጎትዎ ጉግል ምላሽ አለው።
በተለይ የቁጥር ዕጣ ለማውጣት "random number generator" ብለው ይጻፉና ቁጥሮችን የት ማስቀመጥ እንዳለብዎ ይመለከታሉ። "Generate" የሚለው ላይ ከተጫኑ የቁጥር ሥርዓቱ የሚፈልጉትን ያህል ድንገቴ ቁጥሮችን ያወጣል።
ልብ አንጠልጣይ በሆነ መልኩ አዝናኝ ማድረግ ከፈለጉ ደግሞ "spinner" ብለዉ ይጻፉና በቀኝ በኩል የሚታየውን "Number"ን ይምረጡ። ከዚያ እስከ 20 ቁጥሮችን የሚያስቀምጡበት ቦታ ይመጣል። "Spin"ን ተጭነው ውጤቱን ይመልከቱ። ጉግል የዕድለኛ ቁጥሮችን ያወጣልዎታል።
በመቀጠል "Face or cross" ብለው ጽፈው ይመልከቱ፤ ጉግል ያሉትን ዕድሎች ለማሳየት ሳንቲሞች ሲወረውር ይመለከታሉ።
2.ከባድ የሂሳብ ስሌቶችን መፍታት
የመፈለጊያ ሳጥኑ ላይ "calculator" ብለው ከጻፉ መሰረታዊውን ካልኩሌተር ሊያገኙ ይችላሉ። ነገር ግን መስራት የሚፈልጉት የተወሳሰበ የሂሳብ ስሌት ከሆነ ትክክለኛ ቀመሩን (formula) በትክክል ያስቀምጡ።
ውጤቱን ማምጣት የጉግል ፋንታ ይሆናል ማለት ነዉ። ለምሳሌ የሚከተለውን ስሌት ብናስቀምጥ ወዲያውኑ እንዴት ግራፍ ስሎ ሊያሰቀምጥ እንደሚችል እናያለን። cos (12x) + sin (8x)

የፎቶው ባለመብት, Google
3.መለኪያዎችንና የመገበያያ ገንዘቦችን ለመቀየር
"Conversion of measures" ብለው ይጻፉ። ከዚያ በኋላ መቀየር የሚፈልጉትን ርቀት፣ ስፋት፣ የሙቀት መጠን፣ ይዘት እና የተለያዩ መጠኖችን የሚያወዳደሩበትን ካልኩሌተር ያገኛሉ።
"Currency converter" ብለው ከጻፉ ደግሞ የተለያዩ ሀገራትን የመገበያያ ገንዘብ ንጽጽር በቀላሉ ማወደደር ይችላሉ።
4.በዘፈኖች ምት መካከል ምልክት ለማስቀመጥ
ሙዚቀኛ ከሆኑ ይህ መተግበሪያ የሜሎዲ ጊዜን ለመለየት እጅግ ጠቃሚ ነው።
"Metronome" ብለው ይጻፉና የሚመጣውን ምልክት በማየት እያዳመጡ ምቶችን በየደቂቃዉ እንዴት መጨመርና መቀነስ እንደሚቻል መማር ይችላሉ።
5.የሚመችዎትን የሙዚቃና ዘፋኝ ለማግኘት
የአንድን ሙዚቀኛ ስምና የአንድ ዘፈኑን ርዕስ ይጻፉ። ውጤት ማሳያ ሳጥኑ ላይ "Other versions of this song" የሚል ምርጫ ያግኛሉ።
እዚሁ ላይ ሲጫኑ ታደያ ይህን ዘፈን የዘፈኑትን አርቲስቶች ዝርዝር የሚያሳይ የዩቲብ ዝርዝር ያገኛሉ። የሚመችዎትን ሙዚቃና ዘፋኝ በቀላሉ በዚህ መልኩ ማግኘት ይችላሉ። ለምሳሌ ይህን ይጻፉና ይሞክሩ "John Lennon Imagine"

የፎቶው ባለመብት, Google
6.እረፍት ለመውሰድ
ብስጭት ወይም ጭንቀት ተሰምቶዎታል? እንግዲያውንስ "breathing excercise" ብለው ጉግል ላይ ይጻፉ ለተወሰኑ ደቂቃዎች የሚያዝናናዎት እና ቀለል ያለ ስሜት እንዲሰማዎ የሚያደርግ ሰማያዊ ሳጥን ይመጣልዎታል።
7.በቪዲዮ ጨዋታዎች ለመዝናናት
ቀላል የቪዲዮ ጨዋታዎችን መጫዎት የሚፈልጉ ከሆነ "Google Pacman" ብለው ጉግል ላይ ይጻፉ።
ምርጫዎ ሌላ ጨዋታ ከሆነ ደግሞ "Atari Breakout" ብለዉ ይፈልጉ። በተጨማሪም "Snake" ብለዉ ከጻፉ በዝነኛውን "Snake" ጨዋታ መዝናናት ይችላሉ።












