እያነጋገረ ያለው የአማራ ክልል የቤተሰብ ዕቅድ ደብዳቤ

የአማራ ክልል ጤና ቢሮ

ባለፉት ጥቂት ቀናት ከአማራ ክልል ጤና ቢሮ ስለ ወጣ አንድ ደብዳቤ ብዙዎች ብዙ ነገር እያሉ ነው።ደብዳቤው በአማራ ክልል የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት አሰጣጥን የሚመለከት ሲሆን ከደብዳቤው ሃሳብ በመነሳት በክልሉ ሴቶች በተለያየ መንገድ የወሊድ መቆጣጠሪያ እንዲጠቀሙ ግፊት እየተደረገባቸው ነው የሚሉ ሃሳቦች አይለዋል።

የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ታሪኩ በላቸው ደብዳቤው ሁሌም ከቢሯቸው ከሚወጡ ደብዳቤዎች የተለየ ነገር እንደሌለው ፤ ይልቁንም የደብዳቤውን ሃሳብ በተሳሳተ መንገድ የመረዳት ችግር እንደገጠመ ይናገራሉ።

ከሁሉም በላይ በክልሉ አንዳንድ የጤና ፕሮግራሞችን በጥርጣሬ የማየት ነገር እንዳለ ይህም ከፍተኛ ችግር እስከመፍጠር እንደደረሰ የሚናገሩት ሃላፊው ባለፈው ዓመት በክልሉ ጥናት ለማድረግ ወደ ክልሉ የሄዱ ሁለት ምሁራን መገደልን በዋቢነት ይጠቅሳሉ።

"ይህን ሁሉ ያመጣው የክልሉ ጤና አገልግሎት ላይ ጥርጣሬ መኖሩ ነው። ክትባት፣ የህናቶች ጤና አገልግሎትንና ሌሎችንም አገልግሎቶች ያለመጠቀም ችግርም አለ " በማለት ጥርጣሬው በጣም በሚያሰጋ ደረጃ ያለ እንደሆነ ያመለክታሉ።

በጤና አገልግሎት አሰጣጡ ጉድለቶች ካሉ ለማስተካከል፣ አገልግሎቱን በሚመለከት አለመረዳትና የግንዛቤ ችግር ካለም ማስተማር ማስረዳት አስፈላጊ ነው ብሎ በማመን ከህብረተሰቡ ጋር ውይይት ተደርጎ እንደነበር አቶ ታሪኩ ይናገራሉ። በተጨማሪም በዚህ አመት የማህፀን በር ካንሰር መከላከያና የኩፍኝ ሁለተኛ ዶዝ ክትባቶች ለመስጠት ታስቦ ስለነበር ለዚህም ከማህበረሰቡ ጋር የተደረው ውይይት በእጅጉ አስፈላጊ ነበር ይላሉ።

እናም በማህበራዊ ሚዲያ ብዙ የተባለበት ደብዳቤ ከማህበረሰቡ ጋር የተደረገውን ውይይት ተከትሎ የተፃፈ ነው ይላሉ አቶ ታሪኩ።

እሳቸው እንደሚሉት በውይይት መድረኮቹ የሃይማኖት አባቶች፣ አክቲቪስትና የሚዲያ ባለሙያዎች ስለ ስነተዋልዶ ጤና አገልግሎት አሰጣጥ ብዙ ያነሷቸው ጥያቄዎች ነበሩ። "ስምንቱ ነጥቦች ብቻ ሳይሆኑ የተነሱ ሌሎች ጉዳዮች ነበሩ።እኛ በጥናት ያገኘነው እና የታመነበት ባይሆንም ማስተካከያ መስጠት አስፈላጊ ነበር" የሚሉት አቶ ታሪኩ የተባሉት ችግሮች እውነትም ካሉ ማስተካከያ ሊደረግ ይገባል በሚል መንፈስ አቅጣጫ ለመስጠት ደብዳቤው መጿፉን ያስረዳሉ።

ደብዳቤው ለሁሉም የዞን ጤና መምሪያዎች የተፃፈ ሲሆን መምሪያዎቹ ደግሞ ለወረዳዎች እንዲያወርዷቸው ተደርጓል።

በጥቅሉ በክልሉ የጤና አገልግሎት አሰጣጥ ላይ አሉ የሚባሉ ችግሮች ካሉ እንዲስተካከሉ አቅጫ የሚሰጥ ደብዳቤ እንደሆነና ምንም የተለየ ነገር እንደሌለው አቶ ታሪኩ ያስረግጣሉ።

በደብዳቤው ላይ የተነሳ ሌላው ጉዳይ ደግሞ የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት ተጠቃሚ የሚሆኑ ሴቶች ቁጥርን የሚመለከት ሲሆን በቁጥር ደረጃ ይህን ያህል ሴቶችን የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት ተጠቃሚ ማድረግ ተብሎ ሲቀመጥ ለእቅድና አማራጮችን ለማስቀመጥ እንጂ የግድ ይህን ያህል ሴት ተጠቃሚ ይሆናል በሚል እንዳልሆነም አቶ ታሪኩ ያስረዳሉ።