በማሌዥያ ልጃቸውን አንገላቱ የተባሉ ሩሲያዊያን በፖሊስ ተያዙ

ልጃቸውን ወደላይ ሲወረውሩ የሚያሳይ

የፎቶው ባለመብት, FACEBOOK/ZAC.ABDULCHEAH

ሁለት ሩሲያዊን ማሌዢያ ውስጥ ጎዳና ላይ የህጻን ልጃቸውን እግር በማንጠልጠል ወደ አየር ላይ እየወረወሩ በፈጸሙት ትርኢት በፖሊስ ተያዙ።

ፖሊስ ለኤ ኤፍ ፒ የዜና ወኪል እንደተናገረው ጥንዶቹ በአራት ዓመቷ ሴት ልቻቸው ላይ ፈጸሙት በተባለው ማንገላታት ምርመራ ተደርጎባቸዋል።

የጥንዶቹን ድርጊት የሚያሳየው ቪዲዮ ባለፉት ቀናት በስፋት ከተሰራጨ በኋላ ነው ፖሊስ ግለሰቦቹን ይዞ ምርመራ ያደረገው።

90 ሰከንድ የሚረዝመው ቪዲዮ ፌስቡክ ላይ ተሰራጭቶ የነበረ ሲሆን፤ የተመለከቱት ሰዎች "ድርጊቱ ኃላፊነት የጎደለውና ጉዳትን የሚያስከትል ነው" በማለት ፖሊስ ጥንዶቹን መያዝ አለበት በማለት ሲጠይቁ ነበር።

ቪዲዮው አንድ ሰው የህጻኗን እግር በመያዝ ወደፊትና ወደኋላ በማንዠዋዠው ከፍና ዝቅ ሲያደርጋት የሚያሳይ ሲሆን፤ ህጻኗን ወደ አየር ላይ በመወርወር ሲቀልባትም ይታያል።

ፌስቡክ በበኩሉ ቪዲዮውን በተመለከተ በሰጠው ምላሽ ቪዲዮው እንዲወርድና በስፋት እንዳይሰራጭ ያደረገው ድርጊቱ የተፈጸመባትን ህጻን ለመታደግ ይረዳል በሚል እንደሆነ ገልጿል።

ቪዲዮው አሁንም ማንም ሊመለከተው የሚችል ሲሆን "በህጻን ወይም በታዳጊ ላይ የሚፈጸምን ጥቃት የሚያሳይ" ማስጠንቀቂያ አብሮት ቀርቧል።