የኮንጎ ሚኒስትሮች እስከ ህይወታቸው መጨረሻ ደመወዝ እንዲያገኙ ተወሰነላቸው

ጠቅላጥ ሚኒስትር ብሩኖ ሺባላ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ሚኒስትሮቿ እስከ ህይወታቸው መጨረሻ ደመወዝና ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞች የሚያስገኛቸውን ህግአፅድቃለች።

በዛሬው ዕለት በወጣው መንግሥት ባወጣው መግለጫ ይህ ክፍያ የባለስልጣኖቹን ኃብት ለማካበት አይደለም የሚል ነው።

በዚህም መሰረት የቀድሞ ሚኒስትሮች 2ሺ ዶላር (አምሳ ስድስት ሺ ብር) ደመወዝ በየወሩ ይከፈላቸዋል።

ብዙ ደሃ ህዝብ ባለባት የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ይህ መሆኑ ለሰላ ትችት ዳርጎታል።

ስልጣንን በቅርቡ የሚያስረክበው ይህ መንግሥት ይህንን ውሳኔ ያስተላለፈው ሚኒስትሮቹ መሰረታዊ የሆኑ እንደ ምግብ፣ መጠለያና የጤና ሽፋን ግልጋሎቶችን እንዲሸፍንላቸው እንደሆነ ተገልጿል።

መግለጫው ጨምሮ እንደገለፀው ሚኒስትሮቹ ወደ ድህነት እንዳያመሩ ለመከላከል ነው።

በወጪው ጠቅላይ ሚኒስትር ብሩኖ ትሻባላ በህዳር ወር የተፈረሙት እነዚህ አዋጆች የሚዲያውን ቀልብም ሆነ ሽፋን ያገኙት በቅርቡ ነው።

የመጀመሪያው አዋጅ የቀድሞ ሚኒስትሮች አገሪቷን ከሚያስተዳድረው ጠቅላይ ሚኒስትር በ30% ተስተካካይነት ያለው ደመወዝ፣ በየአመቱ አንድ የቢዝነስ የአውሮፕላን በረራ፣ በየወሩ ለቤት የሚሆን 5ሺ ዶላር ብር ክፍያ እንዲፈፀምላቸው የሚያትት እንደሆነ የሮይተርስ ዜና ወኪል ዘገባ ያሳያል።

ሁለተኛው አዋጅ ደግሞ የቀድሞ ሚኒስትሮች አሁን ካሉት ሚኒስትሮች በ30% ተስተካካይነት ያለው ደመወዝ፣ በየወሩ አንድ ሺ ዶላር ለቤት ኪራይ፣በየአመቱ አንድ የቢዝነስ የአውሮፕላን በረራ እንደሆነ ይሄው የሮይተርስ ዘገባ ገልጿል።

ይህ ከፍተኛ ትችት የቀረበበት ህግ ከአገሪቷ ማህበራዊና ኢኮኖሚያው እውነታ ጋር የማይጣጣም እንደሆነ ተገልጿል።

ለአገሪቷ ብዙ ወጭ የሚያስወጣትና የህዝብ ሀብትንም ማባከንም እንደሆነ በመግለፅ የተቹ አሉ።

አዲሱ የዲሞክራቲክ ሪፐብሊኮ ኮንጎ ፕሬዚዳንት ፌሊክስ ትሽኬዲ ቃለ መሐላቸውን የፈፀሙት ባለፈው ወር ሲሆን፤ በስድስት አስር የኮንጎ አመታት ታሪክም ውስጥ ስልጣን በሰላም ሲሸጋገር የመጀመሪያው ነው።

ይህም ቢሆን የምርጫው ውጤት ከትችት ያላመለጠ ሲሆን በአዲሱ ፕሬዚዳንትና በቀድሞው ፕሬዚዳንት ጆሴፍ ካቢላ መካከል ሚስጥራዊ ስምምነቶች ተደርሰዋል የሚሉ ውንጀላዎች ተሰንዝረዋል።

ሁለቱም ግን ውንጀላውን አጣጥለውታል።