ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ በፓርላማው ያነሷቸው ቁልፍ ጉዳዮች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

የፎቶው ባለመብት, PM OFFICE FB

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ አምስተኛ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለአራተኛ ዓመት የመንፈቅ እረፍት ከመውጣቱ በፊት ሁለተኛ ልዩ ስብሰባውን አካሂዶ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ከሕዝብ እንደራሴዎች በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል።

በአገሪቱ የተለያዩ ቦታዎች የሚታዩ ግጭቶች እና ከዚህም ጋር ተያይዞ የሚስተዋለው የተፈናቃዮች ቁጥር ማሻቀብ፣ የታጠቁ ኃይሎች እና ከውጭ የተመለሱ የፖለቲካ ቡድኖች እንዲሁም የህግ የበላይነት የማስከበር አቅም እንደራሴዎቹ ያጠነጠኑባቸው ጉዳዮች ሲሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትሩም በጉዳዮቹ ላይ ምላሽ ሰጥተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምላሻቸው የዲሞክራሲ ምጥ እና ውልደት ህመሞችን ነቅስዋል፤ የሃሳብ ልዕልናን ፈዋሽነት ደጋግመው አውስተዋል፤ የኋላ ቀርነት መገለጫ ናቸው ያሏቸውን በአንድ አካባቢ አናሳ ቁጥር ያላቸውን ማኅበረሰቦች ማጥቃትን እና ዜጎችን ማፈናቀልን አምርረው ወቅሰዋል።

"የፖለቲካ ምህዳሩ ሰፍቷል፤ ይህም ረጅም ርቀት መሮጥ የማይችሉት ትንፋሽ ያጥራቸዋል ማለት ነው" ብለዋል።

ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የተነሱ ጥያቄዎች

ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ከምክር ቤቱ አባላት ተደጋግመው ከተነሱ ጥያቄዎች መካከል፤ በበርካታ የአገሪቱ አካባቢዎች ሲለኮሱ የሚታዩትና ለብዙዎች ሞት እና መፈናቀል ምክንያት የሆኑት ግጭቶች ይገኙበታል።

ከእንደራሴዎቹ መካከል የተወሰኑት በጥያቄዎቻቸው በአንድ በኩል ጠቅላይ ሚኒስትሩን ወደ ስልጣን ያመጣው እና ከዚያም በኋላ ልዩ ልዩ የመንግሥት እና የማኅበረሰብ ፈርጆችን የነካውን ለውጥ ለመቀልበስ ይጥራሉ ያሏቸውን እና በስም ለይተው ያላነሷቸውን ኃይሎች ተጠያቂ በማድረግ ይሄንን ለማስቆም መንግሥት ምን እያደረገ እንዳለ እንዲያስረዷቸው ጠይቀል።

ሌሎች የምክር ቤቱ አባላት ደግሞ መንግሥት የምህረት አዋጅ መደንገጉን፣ መቀመጫቸውን በውጭ አገራት አድርገው የነበሩ የፖለቲካ ቡድኖች እንዲመለሱ ጥሪ ማቅረቡንም ተከትሎ ከተመለሱ ቡድኖች መካከል ነፍጣቸውን እስካሁንም ያነገቡ መኖራቸው ለግጭቶች መፈጠር አስተዋፅዖ ማድረጉን አንስተዋል። እነዚህ ቡድኖች በትክክል የሰላማዊ ትግል ግብዣውን ተቀብለዋል ማለት ይችላል ወይ ሲሉ ጥያቄ ወርወረዋል።

መፈናቀል

"ሰዎችን ከአንድ አካባቢ ልቀቁ ብሎ ማፈናቀል የሥነ ምግባር ልምሻን ከማመላከቱም ባሻገር ኢሕገ-መንግሥታዊ ጭምር ነው" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ፤ ከለውጡ በኋላ ከተፈናቀሉ ዜጎች መካከል ብዙዎቹ ወደቀያቸው መመለሳቸውን ተናገረዋል።

ያልተመለሱትን በተመለከተ ይሄንን ጉዳይ የሚያጠና ኮሚቴ ተቋቁሞ በአትኩሮት እየተከታተለው እንደሚገኝም ገልፀዋል።

የግጭት እርሾዎች ከመብላላታቸው በፊት ለማምከን መስራት፤ ግጭቶች ከተከሰቱ በኋላ እነርሱን ለማክሰም ከመሯሯጥ የበለጠ ተመራጭ አንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለምክር ቤቱ አባላት ነግረዋቸዋል።

የፖለቲካ ቡድኖች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ስለታጠቁ የፖለቲካ ቡድኖች የቀረበላቸውን ጥያቄ ለመመለስ በበዓለ ሲመታቸው ወቅት አድርገውት የነበረውን ንግግር አጣቅሰዋል።

"ዲሞክራሲን ለመፍጠር መንግሥት ዋነኛው አውታር ስለሆነ ሆደ ሰፊ መሆን አለበት" ሲሉ መናገራቸውን ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ሃያ የሚጠጉ የታጠቁም ያልታጠቀሙም ቡድኖች መመለሳቸውን ይህም ትልቅ ድል መሆኑን ጨምረው ተናግረዋል።

ከእነዚህ ቡድኖች መካከል የሚበዙቱ ያሉባቸውን የገንዘብ፣ የጽህፈት ቤት እና የመሳሰሉ ችግሮች ተቋቁመው በሃገሪቷ ውስጥ በዲሞክራሲ ግንባታው የድርሻቸውን ለመወጣት ሃቀኛ ጥረት እያደረጉ ቢሆንም "በጉራማይሌ የፖለቲካ የተጠመዱም" አሉ ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ስም ሳይጠቅሱ ወቀሳ ሰንዝረዋል።

እነዚህን "አንድ እግራቸው አዲስ አበባ አንድ እግራቸው ውጪ" የሆነ ነው ያሏቸው ቡድኖች አካሄድ "ለድል አያበቃም" እንዲያወም የዲሞክራሲን እርምጃ "ወደኋላ ይመልሳል" ሲሉ ነቅፈዋል።

ሃሳብ አጠር ናቸው ያሏቸውን ፓርቲዎች "በመቶ ሜትር ውስጥ ሩጫ የለመዱ ፓርቲዎች ማራቶን ሲሆን ትንፋሽ ያጥራቸዋል" ሲሉ ወቅሰዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይእና አፈ ጉባኤ ታገሰ

የፎቶው ባለመብት, PM OFFICE FB

መንግሥታቸው ለሁሉም የሚሰራ የሰላምን መርህ የተከተለ ጥሪ እንዳቀረበ ገልፀው፤ አስፈላጊ ሲሆን የትዕግስቱን ያህል መረር ያለ እርምጃ ሊወስድ እንደሚችልም አስጠንቀቀዋል።

በሚቀርብለት ጥሪ ወደ ተለያዩ ክልሎች ሰላም ለማስፈን የሚገባው የመከላከያ ሠራዊትን በስኬታማነቱ ያሞካሹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የኢትዮጵያን ሉዐላዊነት የሚገዳደር እንቅስቃሴ የሚያደርግ አካልም ጦርነት እንዳወጀብን እንቆጥራለን ብለዋል።

በሃገሪቱ ያሉ የፖለቲካ ቡድኖች የውስጥ ዲሞክራሲያቸውን እንዲያጎለብቱ ምክር የለገሱት ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ "በራሱ ፓርቲ ላይ ያልተለማመደውን ዲሞክራሲ ኢትዮጵያ ላይ መለማመድ አይችልም" ብለዋል።

ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት

"የከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን እንደጦር መናኸሪያ የመጠቀም አዝማሚያ እንደሚኖር አስቀድሞም እናውቅ ነበር" በዩኒቨርሲቲ ውስጥ ስለሚከሰቱት ችግሮች ምላሽ የሰጡት ጠ/ሚ ዐብይ "ይህንም ስለምናውቅ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት አድርገናል፤ ለተማሪዎቹም በብዙሃን መገናኛ አውታሮች መልዕክት አስተላልፈናል" ብለዋል።

ወጣት ተማሪዎች "ለፖለቲካ አጀንዳ ማስፈፀሚያ" ህይወታቸውን መገበራቸውን "አሳዛኝ" እና "አስነዋሪ" ነው ብለዋል።

አክለውም "ድንጋይ እና ድንጋይ አጋጭቶ እሳት ማውጣት የጋርዮሽ ዘመን ፈጠራ ነው። የምንፈልገው ሃሳብ እና ሃሳብ የሚያጋጭ ተማሪ ነው" ብለዋል።

ሕገ ወጥ የጦር መሳሪያና የገንዘብ ዝውውር

በሌላ በኩል መቼም ኮንትሮባንድ ለሰላማችም ለምጣኔ ኃብትም ስጋት እንደሚሆን ታሰቦ እርምጃ መውሰድ መጀመራችን ለጉዳዩ እንደ አዲስ ትኩረት እንዲሰጥ አድርጎታል ሲሉ ተናግረዋል።

እንደተበራከተ ከሚገለፀው የጦር መሣርያዎች እና የገንዘብ ዝውውር ጋር ተያይዞም ጥያቄ የቀረበላቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የትርፍ ፍላጎት ሻጮችን፣ የደህንነት ስጋት ሸማቾችን ወደ መሳርያ ንግድ እንደሳበ አስረድተው "ሰላምን የማደፍረስ ፍላጎት ያላቸው" ኃይሎችም ይህን እንቅስቃሴ አባብሰውታል ብለዋል።

አገሪቱ ውስጥ ሕገ-ወጥ የጦር መሣርያ መኖሩን የሚገልፁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ "ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የጦር መሳርያ ከህዝቡ ቁጥር በላይ ነው" ብለው፤ ህጋዊ ቢሆንም እንኳ የጦር መሣርያ መብዛት መዘዙ እንደሚከፋ ስጋታቸውን ገልፀዋል።

ስላልተያዙ ሰዎች

ህግ የሚፈልጋቸውን ወንጀለኞችን መያዝ ለምን ከበደ? ክልሎች ወንጀለኞችን አሳልፈን አንሰጥም የማለት ስልጣናቸው ምን ያህል ነው? ተብለው የተጠየቁት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ "ኢትዮጵያ ውስጥ ወንጀል ሰርቶ፤ መንግሥትም ይሄንን ነገር አውጆ ያልታሰረ ወንጀለኛ የለም። ልዩነቱ በእኛ እስር ቤት ውስጥ ነው ወይንስ በራሱ የሚለው ነው" ሲሉ ምላሻቸውን ጀምረዋል።

"ሁሉም ክልሎች ወንጀለኞችን ለህግ ለማቅረብ ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ ነው" ብለው አሁን የተያዙ ተጠርጣሪዎችን እና ተከሳሾችን በሚመለከትም "የጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ድንገተኛ ቁጥጥር በእስር ቤቶች ላይ አድርጓል። በእኛ እስር ቤት ያሉ ሰዎች ስፖርት ይሰራሉ፣ ያነባሉ፣ ይፅፋሉ፣ በቤተሰብ ይጠየቃሉ። በግል እስር ቤት ውስጥ ያሉት እንደዚህ መሆናቸውን እርግጠኛ አይደለሁም" ብለዋል።

ሰው ገድሎና ዘርፎ ፍርድ ሳያገኝ የሚቀር እንደማይኖር ካስረገጡ በኋላ "በግራም ሆነ በቀኝም ፍርድ አለ" ብለዋል።