ለጎረቤት ልጅ ለወደፊቱ 14 ዓመታት የገና ስጦታ አስቀምጦ የሞተው ግለሰብና ሌሎች አጫጭር ዜናዎች

የፎቶው ባለመብት, Owen Williams
ኢትዮጵያ
• በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልልና ምዕራብ ወለጋ አዋሳኝ አካባቢ መንገድ ላይ የተቀበረ ፈንጂ ፈንድቶ 10 ሰዎች ህይወታቸው አለፈ።
ፍንዳታው የደረሰው ህዝብ ጭኖ በመሄድ ላይ የነበረ ሚኒባስ ላይ ሲሆን፤ ፖሊስ ጉዳዩንም እየመረመረው እንደሆነ የክልሉ ቃል አቀባይ አቶ ዘላለም ጃለታ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ማዳጋስካር
• በማዳጋስካር የሚገኙ ገበሬዎች እየተካሄደ ያለውን ሃገር አቀፍ ምርጫ በመተው ወደ እርሻቸው ተመለሱ።
ምክንያታቸው ደግሞ በጉጉት ሲጠበቅ የነበረውና ከወራት በኋላ የጣለውን ዝናብ ለመጠቀም ነው ተብሏል።
ደቡብ አፍሪካ
• የደቡብ አፍሪካ አቃቤ ህጎች የቀድሞዋ የዚምባብዌ ቀዳማቂ እመቤት ግሬስ ሙጋቤ ላይ ክስ መሰረቱ።
ክሱ ደግሞ ቀዳማዊት እመቤቷ አንዲት ደቡብ አፍሪካዊት ሞዴል ላይ ጥቃት አድርሰዋል የሚል ነው።
ግብጽ
• ግብጻዊቷ የሰብአዊ መብት ተሟጋች አማል ፋቲ ከእስር እንድትለቀቅ የሃገሪቱ ፍርድ ቤት ወሰነ።
መንግስት ጾታዊ ጥቃትን ለመከላከል ምንም እየሰራ አይደለም በማለቷ ነበር ለእስር የተዳረገችው።
ናይጄሪያ
• የናይጄሪያው የቀድሞ መከላከያ ሚኒስትር አሌክስ ባዳ ባልታወቁ ታጣቂዎች ተደገሉ።
የቀድሞው ሚኒስትር ከግል የእርሻ ማሳቸው ሲመለሱ ነው በመኪናቸው ውስጥ ተኩስ የተከፈተባቸው።
ዌልስ
• ዌልስ ውስጥ ለጎረቤቶቹ ልጅ ለ14 ዓመት የሚሆን የገና ስጦታ አስቀምጦ የሞተው ግለሰብ ብዙዎችን አስገርሟል።
የሟች ልጅ ስጦታዎቹን ለሁለት ዓመቷ ህጻን ቤተሰቦች ስታስረክብ ሰፈሩ በሃዘንና በደስታ ተውጦ ነበር ተብሏል።
ደቡብ አሜሪካ
• በደቡብ አሜሪካ ስደተኞችን ድንበር የሚያሻግሩ 49 ህገወጥ አዘዋዋሪዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ።
2 ሚሊዯን ዶላር አብሮ መያዙንም ዘመቻውን ያከናወነው የዓለማቀፉ ፖሊስ ተቋም ኢንተርፖል ገልጿል።
ታይዋን
• ሶስት ቅንጡ ፌራሪ መኪኖችን የገጨው ታይዋናዊ ላደረሰው ጉዳት ማሰሪያ የሚሆን እርዳታ እየጎረፈለት ነው።
የተጎሳቆለ ህይወት የሚመራው ወጣት 12 ሚሊዮን የታይዋን ዶላር ክፈል ተብሎ ነበር።
ሶሪያ
• በሶሪያ ህገመንግስታዊ ጉዳይ ላይ የሚመክሩት ሩሲያ፣ ኢራንና ቱርክ መስማማት ሳይችሉ ቀሩ።
በተባበሩት መንረስታት የተዘጋጀውና በሶሪያ ዘላቂ ሰላም የሚያፈላልገው ቡድን በቀጣዩ ዓመት በድጋሚ ይገናኛል ተብሏል።












