ሙሉ ጥርሷን ያስነቀለችው ሴት ህይወቷ አለፈ

ሬቸል ጆንሰን

የፎቶው ባለመብት, Diana Johnston

እንግሊዝ ውስጥ ሙሉ ጥርሷን ያስነቀለች አንዲት የአእምሮ ህመምተኛ ሴት ከቀናት በኋላ ህይወቷ ማለፉ ተገለጸ።

ሬቸል ጆንሰን ሙሉ ጥርሷ በመበስበሱ በአካባቢው የሚገኝ የጥርስ ህክምና ባለሙያ ሁሉም ጥርሶቿ እንዲነቀሉ ካደረገ በኋላ ወደ ቤቷ እንድትመለስ ለቤተሰቦቿ ተናግሮ ነበር።

ነገር ግን ከሰአታት ቆይታ በኋላ ሬቸል ራሷን ስታ በመውደቋ በድጋሚ ወደ ሆስፒታል ተወስዳ፤ ለቀናት በሞትና በህይወት መካከል ስትታገል ከቆች በኋላ በመጨረሻ ህይወቷ ሊያልፍ ችሏል።

በአካባቢው የሚኖሩ ሌሎች ቤተሰቦችም ተመሳሳይ ክስተት እንዳጋጠማቸው ተናግረዋል። ምንም እንኳን ልጆቻቸው ባይሞቱም፤ ለትንሽ የጥርስ ህክምና ሄደው ሙሉ ጥርሳቸው ተነቅሎባቸው እንደተለመሱ ገልጸዋል።

የሬቸል ቤተሰቦችም ልጃችን ሙሉ ጥርሷ እንዲነቀል አልጠየቅንም ነበር፤ እሷ የአእምሮ ህመምተኛ ስለሆነች ሁሉንም ነገር በራሷ መወሰን አትችልም ሲሉ በሃዘን ተውጠው ሁኔታው ያስረዳሉ።

የጥርስ ህክምና ባለሙያውም የቤተሰቦቿን አስተያየት ሳይጠይቅና ይሁንታ ሳያገኝ ሙሉ ጥርሷን መንቀሉ ተገቢ አይደለም በማለት የእንግሊዝ የጤናና ክብካቤ ቢሮ ጉዳዩን እየመረመረው ነው።

ህክምናው ከተደረገላት አንድ ቀን በኋላ በቤት ውስጥ የምትንከባከባት ነርስ ለእናትየው ደውላ ልጇ ደህና እንዳልሆነችና ምላሷ ማበጡን እንዲሁም ከአፏ አካባቢ ደም እየፈሰሳት እንደሆነ ተናግራ ነበር።

በቀጣዩ ቀን ሁኔታው ሲባባስ እናትየው ወደ ሆስፒታል ብታመጣትም እዛው ሆስፒታል ውስጥ ህይወቷ ሊያልፍ ችሏል።