በጋና የአክራ ዩኒቨርሲቲ የማህተመ ጋንዲን ሐውልት አፈረሰ የሚሉና ሌሎችም

የማህተመ ጋንዲ ሐውልት ሲፈርስ የሚያሳይ

የፎቶው ባለመብት, Emmanuel Dzivenu/Joynews

ኢትዮጵያ

ከወራት በፊት ጥያቄ አለን በማለት ወደ ቤተ መንግስት ካቀኑ ወታደሮች 66 ቱ ላይ ውሳኔ መተላለፉን ፋና ዘገበ።

66ቱ ወታደሮች በቀዳማይ ወታደራዊ ፍርድ ቤት ቀርበው ቅጣት ሲተላለፍባቸው በቀሪዎቹ ላይ ደግሞ አስተዳደራዊ እርምጃ መወሰዱ ተገልጿል።

***

በአዲስ አበባ ለ158 የቀበሌ ቤቶች የይዞታ ማረጋገጫ ሊሰጥ እንደሆነ ፋና ዘገበ።

የመሬት ይዞታ ምዝገባና መረጃ ኤጀንሲ ፤ ይዞታ ማረጋገጡን ከዚህ ወር ጀምሮ በተከታታይ ለአምስት ወራት እንደሚያከናውን አስታውቋል።

ሶማሊያ

የቀድሞ የአልሻባብ መሪ በሶማሊያ በኢትዮጵያ ሰራዊት በቁጥጥር ስር ዋሉ።

የአልሻባብ መስራች የሆኑት ሙክታር ሮቦው ዛሬ ጠዋት በቁጥጥር ስር የዋሉት በባይዶዋ ከተማ ተኩስ ልውውጥ ከተደረገ በኋላ ነው።

ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ

በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ መዲና ኪንሻሳ የምርጫ ኮሚሽን ቅጥር በእሳት ተቃጠለ

ባለስልጣናት እንደገለፁት ትናንት ምሽት በምርጫ ጣቢያው በተነሳው ቃጠሎ የድምፅ መስጫ ማሽኖች ተቃጥለዋል።

የእሳቱ መነሻ ምን እንደሆነ ግን በእርግጠኝነት አልታወቀም።

ጋና

በጋና የአክራ ዩኒቨርሲቲ በቅጥሩ ይገኝ የነበረውን የማህተመ ጋንዲን ሀውልት አፈረሰ

ሃውልቱ የፈረሰው የዩኒቨርሲቲው አንድ ፕሮፌሰር ጋንዲ ዘረኛ ነበሩ በማለት ሃውልቱ እንዲፈርስ ፊርማ ማሰባሰባቸውን ተከትሎ ነው።

ምንም እንኳ ጋንዲ አገራቸው ህንድ ከእንግሊዝ አስተዳደር ነፃ እንድትወጣ ባደረጉት ትግል የነፃነት ተምሳሌት ቢሆኑም ስለ አፍሪካዊያን የተናገሯቸው ነገሮች ለብዙዎች አወዛጋቢ ናቸው።

ፈረንሳይ

ፈረንሳይ ስትራስበርግ በተሰኘው ከተማዋ ሶስት ሰዎችን ገድሎ 12ቶችን ያቆሰለውን የ29 ዓመት ወጣት አፋልጉኝ አለች።

ወንጀለኛው ከአገሪቱ ወጥቷል የሚል ጥርጣሬ ያለ ሲሆን ፈረንሳይ ከጀርመን ጋር የሚያዋስናት ድንበር ላይ ጭምር በመቶዎች የሚቆጠሩ ወታደሮችን አሰማርታለች።

ቱርክ

በቱርክ አንካራ በባቡር አደጋ ዘጠኝ የሚሆኑ ህይወታቸው ሲያልፍ 47 የሚሆኑ መቁሰላቸውን የአገሪቱ ትራንስፖርት ሚኒስትር አስታውቀዋል።

በከፍተኛ ፍጥነት ይጓዝ ነበር የተባለው ባቡሩ ከሌላ ባቡር ጋር መጋጨቱንና ከዚያም ድልድይ ጋር መጋጨቱ ተገልጿል።

ቻይና

ቻይና አንድ የካናዳን ባለሃብትን አሰረች።

የቻይናና የካናዳ ፀብ እየተካረረ ባለበት በአሁኑ ወቅት ከዚህ በፊት የካናዳን ዲፕሎማት ያሰረቸው ቻይና እንደገና ካናዳዊ ባለሃብትን በቁጥጥር ስር አውላለች።

ቻይና ሁለቱንም ካናዳዊያን ያሰረችው ብሄራዊ ደህንነቴን የሚጎዳ እንቅስቃሴ ላይ ተሰማርተው አግኝቼአቸዋለሁ በሚል ነው።