የኤርትራው ፕሬዚዳንት የሞቃዲሾ ጉብኝት

የኤርትራው ፕሬዚዳንት ጉብኝት በሶማሊያ

የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ ዛሬ ወደ ሶማሊያ መዲና ሞቃዲሾ ማቅናታቸውን ቢቢሲ ሶማሊኛ ዘግቧል።

በሁለት ቀን ቆይታቸውም ከሶማሊያው አቻቸው መሀመድ አብዱላሂ ፋርማጆ ጋር ተገናኝተው ይወያያሉ።

ፕሬዚዳንት ኢሳይያስ የህዝባዊ ግንባር ኃርነት ኤርትራ ታጋይ በነበሩበት ወቅት ሶማሊያ ይመላለሱ የነበረ ሲሆን፤ ፕሬዚዳንት ከሆኑ በኋላ ግን የመጀመሪያ ጉብኝታቸው እንደሆነ ተዘግቧል።

የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነትን ተከትሎ ሁለቱ ኃገራት የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው የሚል አቋም ያራምዱ የነበረ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ መንግስት በወቅቱ ስልጣን የነበረው የሶማሊያ ፌደራላዊ የሽግግር መንግሥት ግብዣ ተከትሎ ወደ አካባቢው ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት ያካሄደ ሲሆን፤ ሁለቱም ባላንጣዎች በሶማልያ ተቃራኒ ቡድኖችን ሲደግፉ ነበር።

የኤርትራና የኢትዮጵያ መንግስታት በአካባቢው የሚያደርጉት ጣልቃ ገብነት፤ በብዙ የፖለቲካ ተንታኞች እንደ የውክልና ጦርነት ተደርጎ ነበር የተወሰደው።

ይህንንም ተከትሎ የኤርትራ መንግሥት አልሸባብን እንደሚደግፍ የተባበሩት መንግስታት አጣሪ ኮሚቴ ባቀረበው ሪፖርት መሠረት፣ የፀጥታው ምክር ቤት በኤርትራ ላይ ማዕቀብ የጣለ ሲሆን፣ ማዕቀቡን ለሁለተኛና ለሦስተኛ ጊዜ ማራዘሙም ይታወሳል፡፡

ኤርትራ የሚቀርብባትን ውንጀላ ያልተቀበለች ሲሆን፤ የተጣለባትን ማዕቀብም መሰረት አልባ ስትል አጣጥላው ነበር።

ከአስር ዓመት በላይ የሶማሊያና የኤርትራ ግንኙነት ተቋርጦ የነበረ ሲሆን፤ በቅርብ ጊዜያትም የሁለቱ ኃገራት ግንኙነት በመሻሻል ላይ መሆኑ ተዘግቧል።

የሶማሊያው ፕሬዚዳንት መሀመድ አብዱላሂ ፋርማጆ ኤርትራ ሁለት ጊዜ በመሔድ ከኢሳይያስ አፈወርቂ ጋር ሲገናኙ፤ በባህርዳርም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድን ጨምሮ የሶስትዮሽ ውይይት ማድረጋቸው የሚታወስ ነው።

ፕሬዚዳንት ኢሳይያስ የሶማሊያ ጉብኝታቸውን ካጠናቁ በኋላ ወደ ኬንያዋ መዲና ናይሮቢ እንደሚያቀኑም ተገልጿል ።