ከስም ፊት የሚቀመጡ መለያዎና አንድምታቸው

ሴቶች

ከሰሞኑ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪ ቢልለኔ ስዩም ወ/ሮም ወ/ሪትም አትበሉኝ በስሜ ብቻ ጥሩኝ ስትል ያስተላለፈችው መልዕክት የብዙዎች መነጋገሪያ ሆኗል።

ሃሳቡን የተጋሩት ቢኖሩም የማህበረሰቡን እሴት ማፍረስ ነው ሲሉ የተቃወሙም አልታጡም፤ የጋብቻ ሁኔታን የማይገልፁ አማራጭ ቃላትን ያዋጡ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ታይተዋል።

በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የባህል መምህር ዋልተንጉስ መኮነን (ዶ/ር) በየማህበራዊ እርከኑ፣ በሽግግር ጊዜ የሚሰጡ፣ በሐይማኖታዊ ሥርዓት፣ በአስተዳደራዊ ሥርዓት፣ በሙያ የሚሰጡ ማዕረጎችና ሌሎችም የሚና መገለጫ ማዕረጎች እንዳሉ ያስረዳሉ።

'ልጅ' የመኳንንትና የመሳፍንት ልጆች መጠሪያ እንደነበር እንደምሳሌ ያነሳሉ ለማሳያም ልጅ እያሱን ይጠቅሳሉ።

በማህበረሰቡ ዘንድ ያላቸውን ሚናና ሁኔታ ለማሳየት ተብሎ በዕድሜ ደረጃ ለልጆች የሚሰጥ ስያሜም መኖሩን ይናገራሉ፤ ነገርግን በዘመን፣ በአስተዳደር፣ በማኅበረሰብ አስተሳሰብ ልዩነት ምክንያት የሚሰጡት ማዕረጎች (መለያዎች) ሊሻሻሉ አሊያም ሊለወጡ ይችላሉ።

ሲወርድ ሲወራረድ የመጣው ላላገባች ሴት የሚሰጠው 'ወይዘሪት' የሚለው መለያ እንዲሁም ላገባች ሴት የሚሰጠው 'ወይዘሮ' የሚለው ማዕረግ አሁንም ሰዎች ይጠቀሙበታል።

ከአንድ በላይ የሆኑ ያላገቡ ሴቶችም 'ወይዛዝርት' ሚል መጠሪያ ይሰጣቸዋል።

ይህም የማኅበረሰብ ደረጃና ሚናቸውን ለማሳየት ተብሎ የሚሰጥ ማዕረግ እንደሆነ ይገልፃሉ።

በተጨማሪም መለያዎች በቃላት ባይገለጹም እንደየማኅበረሰቡ ባህል የአካል ክፍሎች ለውጥን፣ የአለባበስ ሥርዓትን፣ አካሄድን፣ የሚይዟቸውን ቁሳቁሶች፣ የፀጉር አሰራርን (አቆራረጥን) በማየት ብቻ የግለሰቦችን የጋብቻ ሁኔታ ማወቅ እንደሚቻል ያስረዳሉ - የባህል መምህሩ ዋልተንጉስ።

በቆየው አባዊ ሥርዓት (ፓትሪያርኪ) የሴቶች ሚና ትዳር መስርቶ ልጅ ማሳደግ አንድ የማህበራዊ ደረጃ ማሳያ መንገድ ነበር ይላሉ፤ ማዕረጉም ይህንን ሙያዋን አመላካች ሆኖ ይመጣል።

በተቃራኒው አሁን ባለው ሥርዓት ደግሞ አንዲት ሴት ተምራ ተመራምራ የሙያ ማዕረግ አግኝታ ሚናዋም እየተለየ አሊያም እየተቀየጠ ይሄዳል።

"አንዳንድ ጊዜ እነዚህ ማዕረጎች የነበረውን ርዕዮተ ዓለምና ያለፍንበትን መንገድ ያሳያል" የሚሉት ዋልተንጉስ (ዶ/ር) እነዚህ መገለጫዎች ከወንዶች ይልቅ ሴቶች ላይ ጎልተው መታየታቸውን ይናገራሉ።

እነዚህ ማዕረጎች ያላቸው ትርጓሜና ሚና እየተለወጠ ሲመጣ መምታታትን ያመጣሉ፤ አሁንም የሆነው ከዚህ ዘለለ እንዳይደለ ይገልፃሉ።

ካላቸውና ከሚኖራቸው ሚና ጋር በተያያዘም ማዕረጉ ሥነ ልቦናዊና ማህበራዊ ተፅዕኖዎች ማሳደራቸው አይቀርም የሚሉት መምህሩ "ለምሳሌ ፆታዊ ግንኙነት መስርተው ላያገቡ ይችላሉ ነገር ግን ሊወልዱ ይችላሉ መለያቸውም ወ/ሪት ይሆናሉ። ከዚህም ባሻገር ፈጥናም ሆነ ዘግይታ ብታገባ አሊያም ከነጭራሹ ጋብቻ ምርጫዋ ባይሆን ተፅእኖ ይኖረዋል።"

ማዕረጎቹ ይፋዊ የጋብቻ ሥነ ሥርዓትን የተንተራሱ በመሆናቸውም ይፋዊ ባልሆነ መልኩ ጋብቻ የሚመሰርቱትን ለመጥራት መደናገርን ይፈጥራሉ።

"አግብተሻል? አላገባሽም?" የሚሉ መጠይቆች መዘውተራቸውም በማህበራዊ ግንኙነትም ሆነ በሥነ ልቦናዊ ሥርዓት የሚያሳድረው ተፅእኖ ቀላል የሚባል አይደለም።

በመሆኑም ቃሉና ሚናውም ከዘመኑ ጋር እየተለወጠ በመምጣቱ የሚያስማማና የሚገልፃቸው አዲስ ቃል ማውጣት ሳያስፈልግ አይቀርም ይላሉ ።

በሌላ በኩል በወሎ ዩኒቨርሲቲ የቋንቋ መምህርና የባህልና ኪነጥበብ ዳሬክተር የሆኑት አፀደ ተፈራ (ዶ/ር) እንደሚሉት ችግሩ ያለው ማዕረጉ ጋር ሳይሆን ማዕረጉን ተከትሎ ከሚመጣው ኋላ ቀር አስተሳሰብ ነው ሲሉ ይሟገታሉ።

መገለጫዎቹ እንደ ማዕረግ የሚሰጡ ሲሆኑ በአካባቢው ባህልም የአንድ ሴት የጋብቻ ሁኔታ ሽግግርን ለማመላከት "እንኳን ከወ/ሪት ወደ ወ/ሮነት አሻጋገረሽ" እንደምትባል ጠቅሰው ማዕረጉም አግብታ በፈታች ቁጥር የሚቀየር እንዳልሆነ ይናገራሉ።

ምን አልባት ያች ሴት በትምህርትና በሙያ በሚሰጡ ማዕረጎች ልትተካው ትችላለች ምክንያቱም ሁለት ማዕረግ በአንድ ጊዜ መጠቀም ስለማይቻል ነው ይላሉ።

ወይዘሪት ለማን የሚሰጥ ማዕረግ ነው?

ወይዘሪት ላላገቡ ሴቶች የሚሰጥ የጋብቻ ሁኔታ ማዕረግ ቢሆንም በቀደመው ዘመን ከጋብቻ በፊት የወሲብ ግንኙነት ያልፈፀመች ሴት መጠሪያነትም ይውል እነደነበር ዶ/ር አፀደ ያስረዳሉ። በእርግጥም ያች ሴት ድንግል እንደሆነች ያመላክት ነበር።

ይሁን እንጂ በአሁኑ ዘመን የፍቅር ጋብቻ የሚል ልማድ በመኖሩ አንዲት የ'ወ/ሪት'ማዕረግ የተሰጣት ሴት የወሲብ ግንኙነት አልፈፀመችም ማለት አይቻልም ይላሉ።

ምንም እንኳን ማዕረጉ የቀደመውን አባዊ ሥርዓት የሚያሳይ ቢሆንም ማዕረጉ በማህበረሰቡ ዘንድ ያላትን የጋብቻ ሁኔታ የሚያመለክት ከመሆኑ የዘለለ ሌላ ተፅዕኖ የለውም ሲሉ ዶ/ር አፀደ የራሳቸውን ተሞክሮ ያነሳሉ። ቃሉን ማስወገድም፤ ሌላ ቃል ለመፍጠር መባዘኑም ከንቱ ነው ሲሉ ያክላሉ።

እርሳቸው በማህበረሰቡ ዘንድ የተቀመጠውን የጋብቻ እድሜ ቢያልፉትም ትዳር አልመሰረቱም ለዚህም የራሳቸው ምክንያትና እምነት አላቸው፤ ወ/ሪት ተብለው ቢጠሩም የተለየ ትርጉም አይሰጣቸውም።

ለማዕረጉ ትርጉም ሰጥቶ ማብሰልሰሉም ሆነ መጠቀሙ እንደ ሴቷ ፍላጎትና እምነት የሚወሰን ነው ይላሉ-ዶ/ር አፀደ።

አንዲት ሴት ያለችበት የጋብቻ ሁኔታ የራሷ ምርጫና ውሳኔ እስከሆነና እስካመነችበት ድረስ ከማህበረሰቡ ለሚመጣው አመለካከት ራሷን እንደ ተበዳይ መቁጠሩ ተገቢ እንዳልሆነ ይገልፃሉ። ስለ ማዕረጉ ሳይሆን እንደ 'ቁሞ ቀር' የሚባሉ የማህበረሰቡን አመለካከቶች መሞገት ያስፈልጋል ሲሉም ያክላሉ።