እንግሊዝ አጭበርባሪ ባለሀብቶችን ቪዛ ልትከለክል ነው

የፎቶው ባለመብት, PA
እንግሊዝ ለከፍተኛ ባለሐብቶች ቪዛን በፍጥነት የምታድልበትን የተሳለጠ አሰራር ለማጤን እንደምትገደድ ተሰምቷል።
እዚህ ውሳኔ ላይ የተደረሰው ከተለያዩ አገራት 'ባለሐብቶች ነን' እያሉ ቪዛና የመኖርያ ፍቃድ የሚያገኙ የውጭ አገር ዜጎች ገንዘብ በማሸሽና ሕገወጥ ገንዘብን ሕጋዊ ለማድረግ የሚሞክሩ ኾነው በመጠርጠሩ ነው።
እስከዛሬ ሲሠራበት የነበረው የቪዛ አሰጣጥ 2 ሚሊዮን ፓውንድና ከዚያ በላይ የሚያሳዩ ባለሐብቶች በተለየ ፍጥነት ቪዛና ሌሎች በእንግሊዝ የመኖር የተመቻቹ ሁኔታዎች እንዲሰናዱላቸው የሚያደርግ ነበር።
ምድብ አንድ ("Tier 1") በመባል የሚታወቀው ኢንቨስተር ቪዛ ሥራ ላይ የዋለው ከ2008 ጀምሮ ሲሆን ዓላማው ከአውሮፓ ውጭ ያሉ ታላላቅ ባለሐብቶች ንዋያቸውን በእንግሊዝ ምድር እንዲያፈሱ ለማበረታታት ያለመ ነበር።
በዚህ አሰራር ከፍ ያለ ገንዘብ ሂሳባቸው ላይ ማሳየት የቻሉ ባለሐብቶች በፍጥነት ወደ እንግሊዝ እንዲገቡና ከአምስት ዓመት በኋላም በቋሚነት እንዲኖሩ ዕድል ይሰጣል።
ኾኖም ይህ አሰራር በሕገ ወጥ መንገድ የተገኘን ገንዘብ ሕጋዊ የማድረግ አንድ ስልት ተደርጎ በመወሰዱና በተጨባጭ ለሥራ ፈጠራ እየሰጠ ያለው ፋይዳ እዚህ ግባ የሚባል ባለመሆኑ ለጊዜው እንዲቆምና ዳግም እንዲጤን ተወስኗል።
"ከዚህ በኋላ ይህንን ልዩ ቪዛ ለግል ጥቅማቸው የሚያዉሉትን አንታገስም። ሕግና ሥርዓት መከበር ይኖርበታል" ብለዋል የኢሚግሬሽን ሚኒስትር ካሮላይን ኖክስ።
ይህ አሰራር ከመጪው አርብ ጀምሮ ኦዲት እስከደረግ ድረስ ላልተወሰነ ጊዜ ዝግ ሆኖ እንደሚቆይ ይጠበቃል።
"ከዚህ በኋላ ሀቀኛ ባለሐብቶች ብቻ ዕድሉን እንዲጠቀሙ ይደረጋል። እንግሊዝ ውስጥ ገብተው ንዋያቸውን ማፍሰስ የሚችሉ ሐቀኛ ባለሐብቶች ብቻ" ብለዋል ሚኒስትሩ።
በ2017 ብቻ ምድብ አንድ ("Tier 1") በመጠቀም አንድ ሺህ የሚሆኑ ባለሐብቶች ወደ እንግሊዝ ገብተዋል። ከእነዚህ ውስጥ የሩሲያና የቻይና ባለሀብቶች በርከት ብለው ታይተዋል።
አመልካቾች ይጠየቁ ከነበሩ መመዘኛዎች መካከል በእንግሊዝ ባንክ ጠቀም ያለ የገንዘብ መጠን ማስቀመጥና "መልካም ባህሪ" የተላበሱ መሆን ነው።
አመልካቾት መመዘኛዎችን ሲያሟሉ ያለ ተጨማሪ እንግልት የ2 ዓመት ከ4 ወር ቪዛ ሲሰጣቸው ቆይቷል። ከዚህም በተጨማሪ ቪዛ ማራዘም ሲፈልጉ ፍላጎታቸው እንዲሟላ ይደረግ ነበር።
ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ ገለልተኛ ኦዲተሮች የአመልካቾችን የገንዘብ ምንጭ እንዲያጣራ የማድረግ ሐሳብ አለ።
የኢሚግሬሽን አማካሪ ኮሚቴ እንዳለው ይህ አሰራር በተጨባጭ ለብሪታኒያ ዜጎች ያመጣው ፋይዳ እምብዛምም ነው። ብዙዎቹ ባለሐብት ነን የሚሉ የውጭ ዜጎች የመንግሥት ቦንድ መግዛት እንጂ ሥራ እየፈጠሩ አይደለም ተብሏል።












