የአማራ ክልል በትግራይ እና አማራ አዋሳኝ አካባቢዎች የሚነሱ ግጭቶች እንዲፈቱ መንግሥት የበኩሉን ሚና እንዲወጣ ጠየቀ

የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በትግራይ እና አማራ አዋሳኝ አካባቢዎች የሚነሱ ግጭቶች በአስቸኳይ እንዲፈቱ መንግሥት የበኩሉን ሚና እንዲወጣ ጠየቀ።
ይህንን የተናገሩት በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ዛሬ መግለጫ በሰጠበት ወቅት ሲሆን ከሰሞኑ አላማጣ ውስጥ የተከሰተው ክስተት ፍትህ የሚሻ ነው ብሏል።
የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የግጭቱ መነሻ የራያ አካባቢ ህዝብ የማንነት ጥያቄ እንደሆነ ጠቅሶ ከህዝቡ ጋር በመነጋገር ህገ-መንግስታዊ ምላሽ ሊሰጠው እንደሚገባም አፅንኦት ሰጥቷል።
መፍትሄው ጥያቄውን ከሚያነሳው የአካባቢው ህዝብ ጋር የሰከነ ውይይት በማድረግ የሃይል እርምጃ መውሰድ አለመሆኑ ሊሰመርበት እንደሚገባ መግለጫው አትቷል።
በአንድ ክልል የሚፈጠር የሰላም መደፍረስ ለአጐራባች አካባቢዎች መትረፉ አይቀርምና የሰሞኑ የትግራይ እና አማራ ክልሎች አዋሳኝ ቦታዎች ችግር ለክልላችንም ትልቅ የፀጥታ ስጋት ነው በማለት መግለጫው ጨምሮ አስታውቋል።
ከዚህም በተጨማሪ በአንዳንድ አካላት ዘንድ በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ለሚፈጠረው ችግር የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስትን መክሰሳቸው መሠረት ቢስ ውንጀላ ነው ያለው መግለጫው ክሱንም እንደማይቀበሉ አስታውቀዋል።
የትግራይ ክልል ችግሩን ለመፍታት በሚያደርገው ህጋዊና ሰላማዊ ጥረት ሁሉ የአማራ ክልል ድጋፍ እንደሚያደርግም መግለጫው ጠቅሷል።
የትግራይ ክልል በበኩሉ የትግራይ ክልል መንግስትና ህዝብ ሰላሙን አስጠብቆ የክልሉን ውስጣዊ ችግሮች ለመፍታት ሌትና ቀን በሚረባረብበት ወቅት የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ባወጣው መግለጫ የትግራይ ክልል በአማራ ክልል ለሰላም ችግር ፈጣሪ መባሏ አሳዛኝና ከትንኮሳ የማይተናነስ ጠብ አጫሪ አቋም ነው ብሏል።
መግለጫው አክሎም "የትግራይ ክልል መንግስትና ህዝብ ለአማራ ህዝቦች ማረጋገጥ የምንፈልገው ለሰላማቸው መረጋገጥ እንጂ በማንኛውም ጊዜ ለፀጥታቸው መደፍረስ ምክንያት ሊሆኑ እንደማይችሉ ነው" ሲል ያትታል።
መግለጫው በመቀጠልም "የተከሰተው ግጭት መነሻው የራያ አካባቢ ህዝብ የማንነት ጥያቄ ሲሆን ይህንን ጥያቄ ከህዝቡ ጋር በመነጋገር ሕገ መንግስታዊ ምላሽ መስጠት እንደሚገባ በአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርትም ሆነ በኢህአዴግ ጉባኤዎች አቅጣጫ መቀመጡን ይታወሳል" ብሏል። ኾኖም ግን "ሕገ መንግስቱ በማንነት ጉዳይ ላይ ያስቀመጠውን ስርዓት በመጣስ በሌላ ክልል የውስጥ ጉዳይ ጠልቃ መግባቱ የሚያረጋግጥ መግለጫ ነው።" ሲል የአማራ ክልል መግለጫን ኮንኗል። አያይዞም በራያም ሆነ በወልቃይት አካባቢዎች ለተፈጠሩ ችግሮችንም የአማራ ክልል መንግስት ኃላፊነቱን መውሰድ ይኖርበታል ብሏል።
መግለጫውን ተከትሎ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስትም ለትግራይ ህዝብ በይፋ ይቅርታ እንዲጠይቅ የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ጠይቋል።












