አሜሪካ ከቻይና የሚገቡ እቃዎች ላይ አዲስ ታሪፍ ጣለች

የሩዝ ሰብል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ሩዝ በዚህኛው የታሪፍ ዙር አሜሪካ ያነጣጠረችበት የቻይና ምርት ነው

የአሜሪካና የቤጂንግ የንግድ ጦርነት እየተካረረ ባለበት በአሁኑ ወቅት አሜሪካ 200 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ የቻይና እቃዎች ላይ አዲስ ታሪፍ መጣሏ ተሰማ።

ከእነዚህ መካከል የእጅ ቦርሳዎች፣ ሩዝና ጨርቃጨርቅ ይገኙበታል።በአጠቃላይ በዚህኛው ዙር አሜሪካ ከቻይና የሚገቡ ስድስት ሺህ የሚሆኑ እቃዎች ላይ ታክስ ጥላለች።

ቻይና ቀደም ሲል አሜሪካ ተጨማሪ ታሪፎችን ልትጥል ብትሞክር አፀፋውን እንደምትመልስ አስታውቃ እንደነበር ይታወሳል።

አዲሱ ይህ የአሜሪካ ታሪፍ ከአንድ ሳምንት በኋላ በ አስር በመቶ ጀምሮ ከዚያም እስከ ሃያ አምስት በመቶ ጨምሮ ተግባራዊ እንደሚሆን ተገልጿል።

ሁለቱ አገራት ስምምነት ላይ ምድረስ እስካልቻሉ ድረስ ይህ ነገር እንደ አውሮፓውያኑ እስከ መጭው ዓመትም ሊዘልቅ ይችላል።.

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ይህ የታሪፍ ዙር ቻይና እያሳየች ላለችው ኢፍትሃዊ የንግድ አሰራር አፀፋ ነው ብለዋል።

ኢፍትሃዊ ከሚሏቸው የቻይና የንግድ ተግባራት መካከል ኩባንያዎቿን መደጎም እና ቻይና ውስጥ በተወሰኑ ዘርፎች የሚሰማሩ የውጭ ኩባንያዎች የግድ አንድ የአገር ውስጥ አጋር እንዲኖራቸው ማስገደድ ይገኙበታል።

" መደረግ ስላለበት ለውጥ በግልፅ አስቀምጠናል።ቻይና ለኛ ፍትሃዊ እንድትሆንም ብዙ እድል የሰጠናት ቢሆንም ቻይና አካሄዷን ለመለወጥ ፍቃደኛ ሳትሆን ቀርታለች "ብለዋል ትራምፕ።

አሁንም ለዚህ እርምጃ ቻይና አፀፋ እመልሳለው ብትል አገራቸው 267 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት እቃ ላይ ሶስተኛውን ዙር ታሪፍ ተግባራዊ ለማድረግ እንደምትገደድ በመግለፅ ቻይናን አስጠንቅቀዋል።

እርምጃው በንድፈ ሃሳብ ደረጃ የአሜሪካ ምርቶች ዋጋ ከምታስገባቸው ቁሶች ዋጋ ጋር ሲነፃፀር ርካሽ እንደሆን በማድረግ ተጠቃሚዎች ዋጋው የሚቀንሰውን የአሜሪካን እቃ እንዲገዙ ያደርጋል።