የውጭ ሀገራት ዜጎች በደቡብ አፍሪካዋ ሶዌቶ ጥቃትን እየሸሹ ነው

የፎቶው ባለመብት, Reuters
አንድ ሶማሊያዊ ባለ ሱቅ «ሊዘርፉኝ ሞክረዋል »ያላቸውን ሁለት ታዳጊዎች «ተኩሶ መትቷል» በሚል የተቀሰቀሰው ግጭት ወደለየለት ዝርፊያ እና የውጭ ሀገራት ዜጎችን ወደ ማጥቃት ርምጃ ስለመቀየሩ ተነግሯል።
የሀገሪቱ ፖሊስ እስከ አሁን ድረስ 27 ሰዎችን በቁጥጥር ስር ያዋለ ሲሆን ጥቃቶቹንም አውግዟል።
በ«ዋትስአፕ» የመገናኛ አውታር የአካባቢው ሰዎች ሶማሊያዊ ተከራዮችን ከቤታቸው እንዲያስወጡ ካልሆነ ግን ጥቃቱ ለእነሱም እንደሚተርፍ ቀን ገደብ የተቀመጠለት የዛቻ መልዕክት እንደተሰራጨም ተነግሯል።
የአከባቢው ነዋሪዎች የውጪ ሃገር ዜጎች የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸውን ምርቶች ይሸጣሉ ሲሉ ይወቅሷቸዋል።
በሶዌቶ ኢትዮጵያዊያንን ጨምሮ ሶማሊያዊያን ፣ዚምባብዌያዊያን እና ፓኪስታንያዊያን ሱቆችን ከፍተው ይሰራሉ።
ጥቃቱን ተከትሎ በንግድ እንቅስቃሴ ላይ የነበሩት እኒህ ወገኖች ጓዛቸውን እየሸከፉ ከስፍራው እየለቀቁ እንደሆነ ተሰምቷል።








