ሽጉጥ ይዘው ለመንቀሳቀስ የተገደዱት ከንቲባ

የፎቶው ባለመብት, Miles Sampa
የዛምቢያዋ ዋና ከተማ ሉሳካ ከንቲባ ማይልስ ሳምፓ በፌስቡክ አድራሻቸው ላይ የለጠፉትን ሽጉጥ ይዘው የሚያሳይ ምስል ለማንሳት ተገደዋል።
''ከዚህ በኋላ ወደ ስራ ስሄድም ሆነ መስክ ስወጣ እንደዚህ ነው እራሴን የምጠብቀው። ትናንት ጥቃት ያደረሳችሁብኝ ሰዎች ማን እንደላካችሁ አውቃለሁ። ምናልባት ጥቃት ቢደርስብኝና ፖሊስ ሊደርስልኝ ባይችል እራሴን ከአደጋ እንደዚህ እከላከላለሁ'' ሲሉ ከምስሉ ግርጌ ላይ አስፍረዋል።
ምስሉ ከሰውዬው የፌስቡክ ገጽ ወዲያው የተነሳ ቢሆንም፤ በርካቶች ምስሉን በተንቀሳቃሽ ስልኮቻቸው ለይ በማስቀረት እየተቀባበሉት ነው።
ከንቲባ ሳምፓ ሽጉጡን ይዘው የተነሱትን ፎቶ በፌስቡክ ገጻቸው ላይ ለማስፈርና ሽጉጥ ይዘው ለመንቀሳቀስ የተገደዱት ከደረሰባቸው ጥቃት ጋር ተያይዞ እንደሆነ ለቢቢሲ ተናግረዋል። ጥቃቱ የደረሰባቸውም በህገወጥ መንገድ መሬት የሚሸጡና የግንባታ ህጎችን የሚጥሱ ሰዎች ላይ በከፈቱት ዘመቻ ምክንያት እንደሆነ ገልጸዋል።
ከዚህ ጋር በተያያዘም ወደ አንድ የግንባታ ስፍራ አቅንተው ድርጅቱ ተገቢውን የግንባታ ፈቃድ የሚያሳይ ዶሴ እንዲያስገባ ጠይቀው ሲመለሱ ሃያ ወጣቶች በመኪና ተከታትለዋቸው ዛቻና ማስፈራራት እንዳደረሱባቸው ለቢቢሲ ገልጸዋል።
''ለህይወቴ እየሰጋሁ ስለሆነ ራሴን የመከላከል መብት አለኝ'' ሲሉ ውሳኔያቸው ትክክል እንደነበረ ተናግረዋል። እንደውም ከዚህ በኋላ ወደ ስፖርት ማዘውተሪያዎች ጎራ እንደሚሉና የሰውነት ብቃታቸውን ለመጨመር እንዳሰቡም ጨምረው ተናግረዋል።












